መስከረም ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአርሲ ነገሌ እሰከ ዛሬ የቀጠለውን ተቃውሞ ተከትሎ የአጋዚ ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ ከ 40 በላይ ሰዎች መግደላቸውንና በርካታ ዜጎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሻላ ወረዳ አጄ ከተማ ደግሞ 48 ሰዎች መገደላቸውንና የአካባቢው አርሶአደር ታጣቂዎች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃም 22 የአጋዚ ወታደሮች መገደላቸውንም ነዋሪዎች አክለው ገልጸዋል ። ህጻናት፣ አዛውንት፣ ነፍሰጡሮች ሳይቀሩ መገደላቸውን ከዚህም በላይ የብሄር ግጭት ለመቀስቀስ መሞከሩንም ነዋሪዎች ተናግረዋል ።
ገዢው ፓርቲ ጥቃቱን የፈጸሙት የታጠቁ ፀረ ሰላም ሃይሎች ናቸው ብሎአል። ኦነግንም ቅስቀሳ በማድረግ ከሷል። በምስራቅ ሸዋ ሊበን ዝቋላ ወረዳ ደግሞ ካለፉት 5 ቀናት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ንቅናቄ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል። 6 የአጋዚ ወታደሮችም ተገድለዋል። የአዱላ ፖሊስ ጣቢያውያ ተቃጥሎአል እስረኞችም አምልጠዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ክላሽ ጠመንጃዎች ህዝቡ እጅ ውስጥ ገብተዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ፖሊሶችም እጃቸውን ለህዝቡ ሰጥተዋል።
በሰንዳፋ ደግሞ ፖሊሶች ሌሊት ቤት እየሰበሩ በመግባት በርካታ ወጣቶችን እያፈሱ ወደ እስር ቤት ወስደዋል። በርካታ ወጣቶች ከአካባቢው መሸሻቸውም ታውቋል።