መስከረም ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከኢሬቻ በአል ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን እልቂት ተከትሎ በኦሮምያ የተቀጣጠለው ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን፣ በምእራብ አርሲ አጄ ከተማ ደም አፋሳሽ ሆኖ መቀጠሉን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ የጦር መሳሪያ የነገቡ ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል ከአጋዚ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውንና ቁጥራቸው 17 የሚሆኑ ወታደሮች መገደላቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።በመጀመሪያው ዙር የመጡ ወታደሮች ጉዳት ከደረሰባቸው በሁዋላ ሌላ ተጨማሪ ሃይል ወደ አካባቢው የመጣ ሲሆን፣ ይህ ሃይል በህዝቡ ላይ በመተኮስ በርካታ ሰዎችን መግደላቸውን ተናግረዋል
የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ ከገዢው ፓርቲ በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም። በኩየራ ሲካሄድ በዋለው ተቃውሞ የከተማው ማዘጋጃ ቤት መውደሙንም ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል። በክልሉ የሚኖሩ የሁሉም ብሄር ተወላጆች በጋራ ከአጋዚዎች ጋር ሲፋለሙ መዋላቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በጅማም የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ በከተማው የሚታየው እንቅስቃሴ መቋረጡን ነዋሪዎች ተናግረዋል
በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ውጥረቱ ዛሬም እንዳለ ሲሆን በሰበታ አካባቢ ወጣቶች በመደራጀት ተቃውሞ አሰምተዋል። በሱሉልታ ደግሞ ነዋሪዎች ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
ባለፉት 3 ቀናት በተካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች 11 ፋብሪካዎችና 60 ያላነሱ መኪኖች መቃጠላቸውን የገዢው ፓርቲ ሚዲያ እየዘገቡ ነው። ከተቃጠሉት ፋብሪካዎች መካከል ሳይገን ዲማ፣ ቱቱ ጨርቃጨርቅ፣ አባቦ ጉና፣ አባቦ ሀይላንድ እና ሮቶ ፕላስቲክን ጨምሮ በጠቅላላው 11 ፋብሪካዎች ናቸው።
በቡሌ ሆራ፣ ገርባ፣ አርሲ፣ አምቦ፣ ወንጂ፣ አለም ገና እና ሌሎችም ቦታዎች የደረሱ ውድመቶች ከፍተኛ ሲሆን፣ የአጋዚ ወታደሮችም በርካታ ሰዎችን በአጸፋው ገድለዋል።
በአዲስ አበባ የህወሃት የንግድ ድርጅቶች የተለየ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ታውቋል። ገዢው ፓርቲ የህዝብን ጥያቄ በአፋጣኝ እንዲመልስ ከተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት ጥያቄ ቢቀርብለትም አሁንም በያዘው አቋም እንደጸና ነው።
በአማራ ክልል ደግሞ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ለመጀመር ወጣቶች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን መጀመራቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ የገዢው ፓርቲ የንግድ ተቋም የሆነውን ዳሸን ቢራን ምርት ላለመቀበል ነጋዴዎች ውሳኔ በማሳለፋቸው፣ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።