ገዢው ፓርቲ የኒዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኞችን ኒዮርክ ላይ ጠርቶ ገለጻ ሰጠ

መስከረም ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ኒዮርክ የሚገኘው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቆንስላ ኒዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት የተባሉት ታዋቂ የመገናኛ ብዙሃንስለኢትዮጵያ መልካም ዘገባ እንዲያቀርቡ ማነጋገሩን አምባሳደር ተቀዳ አለሙ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከላኩት እና ኢሳት እጅ ከገባው የአመታዊ የስራ ሪፖርት ለመረዳት ተችሎአል።

አምባሳደር ተቀዳ New York Times እና Washington Post የተሰኙ 2 የሚዲያ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር አገራችንን የሚመለከት ትክክለኛ ዘገባ እንዲያወጡ ለማድረግ ውይይት መደረጉን፣ በውይይቱም  ኢትዮጵያ  በአካባቢው ብሎም በአህጉሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ጥረት፣ በቅርቡ በተካሄደው የፀጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባልነት ምርጫም ከፍተኛ ድምጽ አግኝታ መመረጧን በዝርዘር እንደገለጹ፣ ይህንን ተከትሎ ከ Washington Post 1 ጋዜጠኛ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጭምር ቃለ-ምልልስ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው  አስፈላጊው ትብብር ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በኤርትራ  ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የተመድ የፀጥታው ም/ቤት ቋሚ አባል ከሆኑ ወዳጅ አገራት ጋር በቅርበት በመስራት፣ የአፍሪካ አባላትን ድጋፍ ለማግኘትና ሌሎች ወሳኝ የሆኑ ቋሚ አባላትንም ለማግባባት በተለያየ ደረጃ በበላይ አለቆች ጭምር ጥረት ተደርጎ የተጣለው ማዕቀብ እንዲራዘም በ14 የድጋፍ ድምጽና በአንድ ድምፅ ተአቅቦ ሊጸድቅ ችሏል ሲሉ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።

የፀጥታው ም/ቤትን በሊቀመንበርነት የምትመራው ግብጽ የም/ቤቱ አባላት በኤርትራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ለማስቻል ማቀዷን የሚገልጽ መረጃ ስለደረሰን ጉብኝቱን ለማስቀረት በሚሲዮኑ በኩል ከፍተኛ ስራ ሰርተናል ሲሉ ያብራሩት አምባሳደሩ፣ የታሰበው ጉብኝቱ ከም/ቤቱ አባላት ተቃውሞ ስለገጠመው እንዲሰረዝ ተደርጓል ብልዋል።

የተመድ ዋና ፀሃፊ አስመራን ይጎበኛሉ መባሉን ተከትሎ ሁኔታውን ለማጣራት ከም/ዋና ፀሃፊው፣ ከፖለቲካ ጉዳዮች ዲፓርትመንት ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶች ጋር በዝርዝር መክረን ፣  በአሁኑ ወቅት በዋናው ፀሃፊ ደረጃ ጉብኝት ለማድረግ ሃሳብ እንደሌለ፣ ነገር ግን የፖለቲካ ዲፓርትመንት ኃላፊው ከመጪው መስከረም በፊት እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ስለሰማን ጉብኝቱ እንዲቋረጥ ጥረታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።