በሰበታ ከተማ 11 ፋብሪካዎች መውደማቸው ተገለጸ

መስከረም 26 ፥ 2009)

ከአዲስ አበባ ከተማ ርቀት ላይ በምትገኘው የሰበታ ከተማ ከቀናት በፊት ተካሄዶ በነበረው ተቃውሞ 11 ፋብሪካዎች መውደማቸውንና የንግድ ተቋማት ዝግ ሆነው መቀጠላቸው ታውቋል።

በቢሾፍቱ ከተማ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ ሰበታ ከተማን ጨርምሮ በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄደ መሰንበቱ ይታወሳል።

ከዚህ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ 11 ፋብሪካዎች እንዲሁም 60 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ፖሊስ ሃሙስ ገልጿል።

የጨርቃ ጨርቅ የታሸገ ውሃ እንዲሁም በፕላስቲክ ማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ የወደሙት ፋብሪካዎች መሆናቸውን ፖሊስ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በከተማዋ የሚገኝ አንድ የቱርክ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሆኑት ፋቲህ መሃመት ያንጊን በበኩላቸው ፋብሪካቸው ከ3 በመቶ በላይ መውደሙን ለቱርክ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በከተማዋና በአካባቢው ጸረ-መንግስት የሆኑ ድምጾች ሲያስተጋቡ እንደነበር ፕሬስ ቲቪ የተሰኘ ጣቢያ ዘግቧል።

ከሰበታ ከተማ በተጨማሪ በጉደር፣ ሆለታና ሌሎች የገጠር መንገዶች ተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ መሰንበታቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልጹ ቆይተዋል።

መንግስት በንብረት ላይ ስለደረሱ ጉዳቶች ማረጋገጫዎችን በመስጠት ላይ ቢሆነም በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን አጠቃላይ መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በቢሾፍቱ/ደብረዘይት ከተማ ደርሶ በነበረው ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት 55 ሰዎች በቻ መሞታቸውን በሰጡት ምላሽ አስተባብለዋል።