በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ክልሉን አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ከቶታል ሲል ኦፌኮ አስታወቀ

 

መስከረም 26 ፥ 2009)

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በኦሮሚያ ክልል ዳግም የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ክልሉን አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ መክተቱንና ድርጊቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ሃሙስ ገለጠ።

በአብዛኛው የክልሉ ዞኖች ውስጥ ህዝባዊ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ መንግስት ተቃውሞን ለመቆጣጠር የሃይል ዕርምጃና የጥይት አማራጮችን እየወሰደ እንደሚገኝ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከኢሳት ጋር በወቅታዊ የኦሮሚያ ክልል ዙሪያ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።

በምስራቅ አርሲ ዞን ስር በምገኙ የሻሸመኔ፣ መቂ፣ አጄ፣ ሻላ፣ እና በሌሎች በርካታ የክልሉ ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞን እያካሄዱ ያሉ ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መሆናቸውን የኦፌኮ አመራሩ ገልጸዋል።

ይሁንና ህዝቡ እያካሄደ ያለው የትግል ስልት አቅጣጫን እንዲስት ለማድረግ በመንግስት በኩል ጥረት እየተካሄደ መሆኑን ያስታወቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና የመገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከቀናት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሃሙስ ለአምስተኛ ጊዜ በምስራቅና ምዕራብ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ለአምስተኛ ቀን መቀጠሉን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

ይኸው ተቃውሞ በመባባስ ላይ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ በሚገኙት የአምቦ ጉደር፣ ዶዳ በርጋ፣ እና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ከረቡዕ ጀምሮ ተቃውሞዎች ማገርሸታቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።

በሃገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች እርሳቸውን ጨምሮ ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርት አመራሮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መምከራቸውንና ሃሳብ መለዋወጣቸውንም የኦፌኮ አመራር አክለው አስረድተዋል።

በቀጣዩ ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝንት ያደርጋሉ ተብለው ከሚጠበቁት የጀርመኗ መራሃሔ-መንግስት አንጌላ ሜርከል ጋር ለመመካከር የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፕሮግራም እንደተያዘላቸውም ለመረዳት ተችሏል።

በመካሄድ ላይ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ የመኖር በዓሉን በመጠበቅና በማክበር ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር መረራ ጉዲና በቃለ-ምልልሳቸው አፅንዖት ሰጥተዋል።