የእስራዔል መንግስት ቤተ-እስራዔላውያን ኢትዮጵያውያን ወደ እስራዔል ማጓጓዝ እንዲጀምር ይፋ አደረገ

መስከረም 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ባለው የጸጥታ ችግር ዜጎች ወደ አማራ ክልል እንዳይጓዙ የሰጠውን የእስራዔል መንግስት ዕሁድ ጀምሮ ቤተ-እስራዔላውያን ኢትዮጵያውያን ወደ እስራዔል ማጓጓዝ እንዲጀምር ሃሙስ ይፋ አደረገ።

የሃገሪቱ ባለስልጣናት ከበጀት ምደባ ጋር በተያያዘ ተፈጥሯል ባሉት ምክንያት ቤተ-እስራዔላውያኑን የማጓጓዙ ሂደት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ከወራት በፊት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ይሁንና የእስራዔል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የፊታችን ዕሁድ በመጀመሪያው ጉዞ 78 ተጓዦች ወደ እስራዔል እንደሚጓዙና አስፈላጊውን ዝግጅት መጠናቀቁን እንደገለፅ ታይምስ ኦፍ እስራዔል የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

በመጀመሪያው ዙሪ ወደ እስራዔል ከሚጓጓዙት መንገደኞች መካከል አብዛኞቹ በእስራዔል መከላከያ ሰራዊት ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ወታደር ቤተሰቦች መሆናቸውን የእስራዔል ልኩድ ፓርቲ ቃል አቀባይ ኒሞሮድ ሳባ ለመገናኛ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ 9ሺ የሚጠጉ ቤት እስራዔላዊያን ወደ እስራዔል ለመጓዝ በጎንደር እና አዲስ አበባ ከተማ እየተጠባበቁ ሲሆን እስራዔል የተቀሩ ሰዎችን ለማጓጓዝ ዝግጅት እያደረገች መሆኑ ታውቋል።

የልኩድ ፓርቲ ቃል አቀባይ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ቤተ-እስራዔላውያኑ ለማጓጓዝ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በታይምስ ኦፍ እስራዔል ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ተጓዦቹን በነሃሴ ወር ለማጓጓዝ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ጉዞው መስተጓጎሉን ለመረዳት ተችሏል።

በቀጣዩ 2017 ዓም 1ሺ 300 ቤተ እስራዔላዊያን ወደ እስራዔል ይጓዛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የተቀሩ መንገደኞችን በሁለት አመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙም ታውቋል።

ከቀናት በፊት በኦሮሚያ ክልል በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የእስራዔል መንግስት ዜጎች ወደ ክልሉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ ማሳሰቡም የሚታወስ ነው።