በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞች ተጠናክረው ቀጥለዋል

መስከረም ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም ፋብሪካዎችና ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከፍተኛ ተቃውሞ በተካሄድባቸው ወንጂ እና ሶደሬ አካባቢዎች  የአጋዚ ወታደሮች በተኮሱዋቸው ጥይቶች ቁጥራቸው በው ያልታወቀ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ የስኳር ፋብሪካው ንብረት የሆነው የሸንኮራ አገዳ እርሻ እንዲሁም የሼክ ሙሃመድ አላሙዲ የከብት እርባታ ድርጅት መውደሙን የካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በሰበታ እና አለም ገና አካባቢዎችም እንዲሁ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን ተከትሎ ሰዎች መገደላቸውንና ፋብሪካዎችም መውደማቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። በቡራዩ ዞን ወደ አሸዋ ሜዳ አካባቢ ከአራት ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል

በጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ያካሂዱ ሲሆን ፣ ህዝባዊ ተቃውሞው ወደ ደቡብ በማምራት በዲላ የጉራጌና ስልጤ ተቀላጆች በጋራ ድምጻቸውን ለማሰማት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት በፖሊሶች ተበትነዋል።

የኢሬቻ በአል እልቂት ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ የታዋቂውን የአፍሪካ ባለሀብት ዳንጎቴ ስሚንቶ ፋብሪካን ፣ የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ የሳይጊን ዲማ እና ቢኤምቲ የሃይል ማስተላለፊያ ገመድ ማምረቻ  ፋብሪካ፣ የተለያዩ አበባ እርሻዎችና ፋብሪካዎች ወድመዋል።