በእሬቻ የተወሰደውን የግድያ ዕርምጃ በተመለከተ ማጣራት እንዲካሄደበት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

ኢሳት (መስከረም 25 ፥ 2009)

በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ የደረሰው ዕልቂትና በተለያዩ ከተሞች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ለመቆጣጠር እየወሰዱት ነው ያለው የሃይል ዕርምጃ ሙሉ ማጣራት እንዲካሄደበት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ረቡዕ ጠየቀ።

የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን ዕርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ያሳሰበው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በተፈጸሙ ግድያዎች ዙሪያ ማጣራት እንዲካሄድበት ግዴታ እንዳለበት ገልጿል።

በቢሾፍቱ ከተማ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ዳግም የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ግድያውን የማጣራቱ ሂደት መካሄድ እንዳለበት ማሳያ መሆኑን ሂውማን ራይትስ ዎች በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

መንግስት በእሬቻ በዓል ስነስርዓት ወቅት የጥይት ድምፅ አለመሰማቱን ቢገልጽም፣ የተለያዩ አካላት የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ እና የአስለቃሽ ጢስ ለመጠቀማቸው መረጃ ማቅረባቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል።

መንግስት ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃ ስለመጠቀሙ ቢያስተባብልም፣ የተለያዩ ማስረጃዎች በእጃን ይገኛሉ ሲሉ በምስራቅ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድና ታላላቅ ሃይቆች ሃገራት የድርጅቱ ምክትል ሃላፊ የሆኑት ሚቼሊ ካጋሪ ተናግረዋል።

የጸጥታ ሃይሎች በቢሾፍቱ ከተማ እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር እየወሰዱት ያለው የሃይል ዕርምጃ በገለልተኛ አካል ማጣራት መካሄድ እንደሚገባው ሃላፊዋ አክለው አሳስበዋል።

የሟቾች ቁጥር በትክክለኛ መንገድ አለመታወቁ እንዲሁም መንግስት እያስተባበላቸው ያሉት ድርጅቶች ገለልተኛ የምርመራ ሂደት እንዲካሄድ ተጨባጭ ምክንያት መሆናቸውን አለም አቀፉ የሰብዓዊ መበት ተሟጋች ተቋም አክሎ አመልክቷል።

ይህይ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት ከቀናት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ በደረሰው አደጋ መዘኑን በመግለጽ በመካሄድ ላይ ያለው ተቃውሞ ዕልባት እንዲያገኝ ጠይቋል።