በኢትዮጵያ ኢንተርኔት መቋረጡን ቢቢሲ ዘገበ

ኢሳት (መስከረም 25 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ማክሰኞ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግልቶ ማቋረጡን የብሪታኒያው አለም አቀፍ የማሰራጫ ጣቢያ (BBC) ረቡዕ ዘገበ። ተቃውሞውን ምክንያት በማድረግ በተወሰደው በዚሁ ዕርምጃ በመደበኛና በተንቀሳቃሽ የስልክ አገልግሎት የኢንተርኔት አገልግሎትን ሲያገኙ የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎቱ እንደተቋረጠባቸው ታውቋል።

በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ የላቀ ነው የተባለን የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት ከኢትዮ-ቴለኮም ጋር ውል የፈፅሙ ተጠቃሚዎች ሳይቀር የኢንተርኔት አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን BBC ረቡዕ በአበይት የአፍሪካ ጉዳዮች ዙሪያ ባቀረበው ዝግጅት አመልክቷል።

ነዋሪነታቸው በመዲናይቱ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች የሆነ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው የኢንተርኔንት አገልግሎት ከሰኞ ጀምሮ መቋረጡን ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የመደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ረቡዕ ቢቀጥልም የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች ከአገልግሎቱ ውጭ መሆናቸውን ከተጠቃውሚዎችና ከBBC መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

በቅርቡ አጨቃጫቂ ነው የተባለ የኢንተርኔት አጠቃቀም አዋጅን ያጸደቀው የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በተደጋጋሚ የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ዕርምጃ ሲወስድ መቆየቱ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መንግስት በአገልግልቱ ላይ በሚወስደው ዕርምጃ በመደበኛ የስራ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮ ማሳደሩን በቅርቡ መግለጹ የሚታወቅ ነው።