በቢሾፍቱ ከደረሰው የሞት አደጋ የተረፉትን ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት በፍለጋ የተሰማሩ ሰዎች ሆስፒታሎችና ፖሊስ ጣቢያዎችን እየጠየቁ መሆኑ ተነገረ

 

ኢሳት (መስከረም 25 ፥ 2009)

ከቀናት በፊት በቢሾፍቱ/ደብረዘይት ከተማ በእሬቻ በዓል ወቅት ከተፈጠረው ዕልቂት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ያልቻሉ በርካታ ሰዎች ለአራተኛ ቀን በከተማዋ በሚገኙ ሆስፒታሎችና ፖሊስ ጣቢያዎች ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸው ታወቀ።

የከተማዋ ሆስፒታል ህክምና የተደረገላቸው ወደ 100 አካባቢ ሰዎች ህክምናቸውን ጨርሰው እንደወጡ ቢያሳውቅም አሁንም ድረስ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ የገቡበት ያልታወቀ የቤተሰብ አባሎቻቸውን በማፈላለግ ላይ መሆናቸውን እማኞች ገልጸዋል።

በሆስፒታል አካባቢ በመገኘት የጠፉ ሰዎችን በመጠየቅ ላይ የሚገኙት እነዚህ አካላት ለእስር የተዳረጉ ሊኖሩ ይችላሉ በማለት ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በመንከራተት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

እሁድ በከተማ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ዕልቂት የሆነውን አደጋ ተከትሎ ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው ፍሪደም ሃውስ የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወቅቱ የተቀሰቀሰን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የከፈቱት የጥይትና የአስለቃሽ ጪስ ለእልቂቱ ምክንያት መሆኑን ማክሰኞ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በእሬቻ በዓል አከባበር ወቅት ምንም አይነት ጥይት አልተተኮሰም ሲሉ ድርጊቱን ቢያስተባብሉም የሟች ቤተሰቦችና እማኞች በጥይት የቆሰሉ ሰዎችን ስለመመልከታቸው ኢሳትን ጨምሮ ለተለያዩ መገኛኛ ብዙሃን ሲገልጹ ቆይተዋል።