መስከረም ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአንቦ ዩንቨርሲቲ ወሊሶ ካንፓስ መምህር እና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ በዓምደ መረብ ጸሃፍነት በመሆን በኢትዮጵያ የሚፈጸሙትን ግድያዎች፣ አፈናዎችና ኢሕገመንግስታዊ የመብት ጥሰቶችን በመጋለጥ የሚታወቀው መምህር ስዩም ተሾመ ከመኖሪያ ቤቱ በደኅነትና በአጋዚ ወታደሮች ታፍኖ ተወስዷል። እስካሁንም ታፍኖ ከተወሰደ ከተወሰደ በኋላ ያለበት ሁኔታ እንደማይታወቅና ለፍርድ አለመቅረቡ እንዳሰጋው ሲፒጄ አስታወቀ።
ስዩም ተሾመ ስለመብት በመጻፉ ብቻ መታሰሩ የጋዜጠኞችን መብት አፈና በኢትዮጵያ አሁንም ተባብሶ በከፋ ሁኔታ መቀጠሉ ያሳያል ሲል ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ሲፒጄ በሪፖርቱ አመላክቷል። እጁ ከተያዘበት እለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ክስ ቀርቦበት ወደ ፍትሕ አካላትካለመቅረቡ በተጨማሪ ከጠበቃው እና ከቤተሰቡ ጋር የመገናኘት መብቱ አልተከበረለትም። የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰቃየት ከሚታወቁት ሶስት አገሮች አንዱ መሆኑን ሲፒጄ ጠቅሶ ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች ተለቆ መደበኛ ስራውን ይጀምር ዘንድ ሲፒጄ ጥሪውን አቅርቧል።
የህወሃት ኢህአዴግ ገዥዎች በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራንን በመጥራት ለማወያየት ያደረጉት ሙከራዎች መክሸፋቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ለመብታቸው ቀናኢ የሆኑ የለውጥ አቀንቃኝ የሆኑ መምህራንን በተናጠል ማሰርና በአሸባሪነት መክሰስ ጀምሯል።