ኢሳት (መስከረም 23: 2009)
ከ30 አመት በላይ በትዳር አብረው የኖሩ ባለቤታቸውንና አንዲት ልጃቸውን በአደጋው ያጡ የሰንዳፋ ከተማ ነዋሪ እሁድ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተወሰደውን ዕርምጃ “የውጭ ወራሪ ሃይል” ድርጊት የሚመስል ነበር ሲሉ ገለጹ።
የዘጠን ልጅ አባት የሆኑትን በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ የሚገኙት አቶ ደረጀ ኡርጊ በሞት የተለዩአቸውን ባለቤታቸውንና የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችን ልጃቸው ከአፍንጫቸው ጥቁር ፈሳሽ ይወጣ እንደነበር ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
በእለቱ በሄሊኮፕተር የታገዘ እርምጃ ሲወሰድ እንደነበር የገለጹት አዛውንት ቢሾፍቱ ከተማ አስከሬን ለመረከብ በሄዱ ጊዜ በርካታ አስከሬኖች መመልከታቸውንና ባዩት ነገር ሊናገሩት ያልቻሉት ሃዘን እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። እሁድ በበዓሉ አከባበር ወቅት የተፈጸመው ድርጊት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የተፈጸመ ድርጊት ይመስል ነበር ያሉት አቶ ደረጀ ኡርጊ ሟች ልጃቸው ከዘጠኝ ልጆቻቸው መካከል ስድስተኛዋ እንደነበረች በሃዘን አስረድተዋል።
ባለቤታቸውንና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው በኦሮሞ ባህል መሰረት የእሬቻ በዓሉን ለመታደም ወደ ቢሾፍቱ ማቅናታቸውን አውስተው በደረሰባቸው ሃዘን የከተማዋ ነዋሪ እያጽናናቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የእኚሁ አዛውንት ባለቤት የልጃቸው የቀብር ስነስርዓት ሰኞ የተከናወነ ሲሆን፣ የአለም መንግስታት ጣልቃ በመግባት “ወረርሽን በሽታ” ሲሉ የገለጹትን የኢህአዴግ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወሰድበት ጠይቀዋል።
ያለ እናት በቀሩ ስምንት ልጆቻቸው የወደፊት ህይወት ሃሳብ ገብቷቸው የሚገኙ እኚሁ አዛውንት ለህዝቡ ኢትዮጵያውያን እንደሚደርሱለት ተማጽነዋል።