በኢሬቻ በአል ላይ የደረሰውን እልቂት ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞች ተካሄዱ

መስከረም ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- መስከረም 22 በቢሾፍቱ በኢሬቻ በአል ላይ በተገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ እልቂት ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው። ዜናው ከፈጠረው ድንጋጤ በተጨማሪ ፣ በበርካታ ከተሞች ህዝቡ ቁጣውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ አርፍዷል።

እናቶችና አባቶች ለኢሳት ስልክ በመደወል ሀዘናቸውን መቋቋም እንደተሳናቸው ሲገልጹ አርፍደዋል። በቡሌ ሆራ መላው የከተማው ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ በመውጣት ተቃውሞውን የመንግስት ድርጅቶችንና መኪኖችን በማቃጠል ተቃውሞውን ሲገልጽ ውሎ አምሽቷል። የህዝቡ ቁጧ ይህን ዜና እስካጠናክረንበት ጊዜ ድረስ አልበረደም።  3 ሰዎች በጥይት መመታታቸውም ታውቋል።

በአምቦ ትናንት የጀመረው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ አንድ ሰው መመታቱ ታውቋል። መኪኖችም ተቃጥለዋል። አንዲት የ4 ወር ነፍሰጡርን ያጣው የጎንጪ ነዋሪዎም ቁጣውን ሲገልጽ ውሎአል።

በቦሌ አራርሳ ከ4 ሺ በላይ የሚሆኑ የኮንዶሚኒየም ሰራተኞች ስራ አቁመው ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ አርፍደዋል። ዝዋይ፣ ሻሸመኔ፣ አጄ እንዲሁም በቢሾፍቱ ህዝባዊ ተቃውሞች ተካሄደዋል።

የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ድርጊቱን ጸረ ሰላም ሃይሎች እንደጀመሩትና ወታደሮች በህዝቡ ላይ አለመተኮሳቸውን ገልጿል። ይሁን እንጅ የአይን እማኞች እንደገለጹት በበአሉ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት አሁን በሰልጣን ላይ ያሉት አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ሳይሆኑ የቀድሞውን የገዳ መሪ ንግግር አቶ  ነገሰ ነገዎ እንዲያደርጉ በመጋበዛቸው ለተቃውሞው መጀመር ምክንያት ሆኗል። ህዝቡ አባገደ በየነ ሰንበቶ እንዲመርቅ ቢጠይቅም ገዢው ፓርቲ ግን ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። አባገዳ በየነ ሰንበቶ በቦታው ላይ እንደነበሩ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል። አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ “ወታደሮችን አንፈልግም ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም ይገባል፣ በአሉ የፖለቲካ በአል ባለመሆኑ ባለስልጣን አንፈልግም”  በማለታቸው በገዢው ፓርቲ በኩል በጥርጣሬ እንዲታዩ አድርጓቸው ነበር።

ወታደሮች አስለቃሽ ጭስና ጥይት ይተኩሱ እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል። በርካታ ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የሞቱ ሲሆን፣ አስከሬን የመፈለጉ ስራ አሁንም እተካሄደ  ነው።