ኢሳት (መስከረም 20 ፥ 2009)
በቅርቡ በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች በስራ ማቆም አድማ ተሳትፋችኋል የተባሉ የንግድ ድርጅቶችን ለማሸግ በንግድ ቢሮ እየተካሄደ ያለው የማሸግ ዕርምጃ ነዋሪዎችን ማስቆጣቱ ታወቀ።
በተለይ ከአንድ ሳምንት በፊት ለሶስተኛ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ውስጥ በቆየችው የጎንደር ከተማ በርካታ ሱቆች እየታሸጉ መሆናቸውን እማኞች ማስረጃዎችን በማስደገፍ ለኢሳት አስረድተዋል።
ይሁንና የከተማው የንግድ ቢሮ የንግድ ድርጅቶቹን ለማሸግ እየወሰደ ያለው እርምጃ በነዋሪዎች ዘንድ ቁጣን እንደቀሰቀሰ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ገልጸዋል።
ሆቴሎችና ሻይ ቤቱን በዚሁ የማሸግ እርምጃ ዋነኛ ኢላማ መሆናቸውን የተናገሩት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ድርጊቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ ህዝባዊ ተቃወሞ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ለኢሳት መረጃን ያደረሱ አካላት አስታውቀዋል።
በሃምሌ ወር በአማራ ክልል በሚገኙ በርካታ ከተሞች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በተለይ በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች የስራ ማቆም አድማዎች ሲካሄዱ መሰንበታቸው ይታወሳል።
ነዋሪዎቹ መንግስት የሚወስደውን የሃይል ዕርምጃ በአስቸኳይ በማቆም ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ሰላማዊ ምላሽ እንዲሰጥ ሲያሳስቡ የቆየ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ተቃውሞው ሙሉ ለሙሉ መረጋጋት አለማሳየቱን ለመረዳት ተችሏል።
የመንግስት ታጣቂ ሃሎች ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር በወሰዱት ተቃውሞ እርምጃ በባህር ዳር ከተማ ብቻ ከ50 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልጹ ቆይተዋል።
አለም አቀስ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተወሰደ የሃይል ዕርምጃ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻሉ።
ድርጊቱ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ጥያቄ ቢቀርብም የኢትዮጵያ መንግስት ተባባሪ እንደማይሆን ይፋዊ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።