የመልቀቂያ ወረቀት ያቀረቡ በርካታ ወታደሮች በመለስ አጽም እየተባሉ እንዲቆዩ እየተለመኑ ነው

መስከረም ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በመላው አገሪቱ የሚታየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የ7 አመታት የከንትራት ጊዜያቸውን የጨረሱ ወታደሮች መልቀቂያ በብዛት እያስገቡ ቢሆንም፣ አዛዦቹ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶ እግራቸው ስር በማንጠፍ “ የመለስን ፎቶ ተራምደኸው እለፍ፣ በመለስ አጽም ይዘንሃል” እየተባሉ ኮንትራታቸውን እንደሚያራዝሙ የመከላከያ ምንጮች ገለጹ”

በአሁኑ ሰአት መከላከያው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ወታደሮች በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የሚካሄዱትን ህዝባዊ አመጾች ፣ “በአማራ ክልል ከሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ገብቶ የህዝብ ንብረት እያወደመ ህዝብ እያተራመሰ ነው ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሆነ ደግሞ ኦነግ ገብቶ ህዝብ እየበጠበጠ ነው ለግዳጅ ተዘጋጁ” እንደሚባሉ ተናግረዋል። ሰራዊቱ ወደ ቦታው ደርሶ ሁኔታውን አጣርቶ የራሱን ግንዛቤ እንዳይዝ ለማድረግ ኔት ወርክ እንደሚዘጉበትና ከሌላው ህዝብ ጋር እንዳይገናኝ እንደሚያደርጉት እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል። በዚህ የተሳሳተ መረጃ  ወታደሩን ከእህት፣ ወንድሙ እናት እና አባቱ ጋር እያዋጉት ነው በማለት ሰራዊቱ ስለገጠመው ፈተና ይገልጻሉ። ሁኔታውን ዘግተውም ቢሆን የተረዱ ወታደሮች መልቀቂያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከአቀጣጠሩ ጀምሮ እየተሰራ ያለውን ደባም በዝርዝር ይናገራሉ። መጀመሪያ አንድ ወጣት ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ለማስገባት ሲመለምሉ ጤና ሳይንስ፡ ኮምፒውተር ሳይንስ፡ ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉትን ትማራላችሁ ብለው በማታለል መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ በሁዋላ ላይ ትምህርቱን የሚማረውና አየር የሚያበረው ግን አብዛኛው የህወሃት አባላት ብቻ ናቸው ይላሉ።

ሰራዊቱ በመጀመሪያ የፈረመውን የ7 አመታት ኮንትራት በአነስተኛ የደሞዝ ክፍያ ቢጨርስም፣ ኮንንትራቱ ካለቀ በሁዋላ ግን አብዛኛው መልቀቂያ እንደሚያስገባ ይገልጻሉ።

ቀድም ብሎ “አንፈልግም” የሚሉትን ወታደሮች  ባንዲራ እያነጠፉ “ አልፈልግም ካልክ ባንዲራውን እረግጠኸው ሂድ” የሚል አሰራር ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን፣ አንዳንድ ወታደሮች በምሬት እና በንዴት  ወደ ቤተሰቤ መሄድ እፈልጋለሁ ብለው ባንዲራውን ተራምደው ሲያልፉ በጠላትነት ተፈርጀው ሰባት ዓመት እንዳላገለገለ ሁሉ  ወደ ወታደራዊ እስር ቤት ይወረወራል ይላሉ ፡፡

በአገሪቱ የሚታየው ችግር እየተባባሰ መምጣቱንና የስርዓቱን ባንዲራ እየተራመዱ የሚሄዱ ወታደሮች መበራከታቸው ያሳሰባቸው አዛዦች፣ ከባንዲራው የበለጠ ጉልበት ይኖረዋል ብለው የሚያስቡትን የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ በመያዝ ፣ በመለስ አጽም እያሉ በመለመን ላይ ናቸው። በአካል ብቃት ችግር ወይም በህመም ሲሰናበቱም አንድ አመት ላገለግሉበት 1 ሺ ብር በአጠቃላይ ለ7 አመታት አገልግሎት 7 ሺ ብር ብቻ ተሰጥቷቸው እንደሚሰናበቱም ገልጸዋል።

ከወታደራዊ ማሰልጠኛ እስከ ዋናው የጦር ክፍል ድረስ የሚዘመረው ስለ ህወሓት ጀግንነት መሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ በብሄር የተነሳ የበላይነትና የበታችነት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚሰራ በመሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ ለሚታዬው ክፍፍል አንዱ ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከዋናው ኢታማዦር ሹም ሰሞራ የኑስ ጀምሮ የ4ቱም ዕዝ አዛዦች፣ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ የ2ቱም ካምፓስ አዛዦችና አመራሮች እንዲሁም የጦር ማሰልጠኛ ክፍሎችና የክፍለ ጦር አዛዦችና አመራሮች በሙሉ ይህን የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በንቃት እንደሚሰሩ ይገልጻሉ።

አብዛኛው ስልጣን አልባ የተደረገው ታዛዡ ወታደር ወር ሃዊ ደሞዙን እንኳ በወጉ እንዳይገኝ በሰበብ አስባቡ እንዲቆረጥበት መደረጉ ለተጨማሪ ብሶት ዳርጎታል።

አንድ ወታደር ግዴታ በ6 ወር አንድ ጊዜ የወታደራዊ ሬንጀር አልባሳትና ከስክስ ጫማ  አሟልቶ መግዛት ግዴታው እንደሆነ የሚገልጹት ወታደራዊ ምንጮች፣ ልብስና ጫማ አንድ ጊዜ ለመግዛት የ2 ወር ደመወዙን እንደሚያጣ፣ “ሰራዊት አይደለም ብሩን ህይወቱን እየለገሰ ነው” በሚል ቅስቀሳ ደግሞ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በየዓመቱ የ1 ወር ደመወዙን እንዲከፍል መደረጉ ፣ ወታደሩ በዓመት የ7 ወር ደመወዝ ብቻ እያገኘ ህይወቱን እንደገፋ መደረጉ  እንዲሁም በውጭ ሀገር ሰላም አስከባሪ እየተባለ በዳርፉር፡ በአብይ ግዛትና በሶማሊያ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የሚያመጣው ገንዘብ አብላጫው ፐርሰንት ለመንግስት ግብር እየተባለ እየቆረጠ ለህወሓት ጀኔራሎች  ቤት መስሪያና ለመኪና መግዢያ  መዋሉ ወታደሩ በብዛት እየለቀቀ እንዲሄድ ተጨማሪ ምክንያት ነው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የትግራይ ተወላጅ የአጋዚ አባል፣ “በህዝቡ ላይ በወሰድኩት እርምጃ ተጸጽቻለሁ፣ ከዚህ በሁዋላ ግን ይህን ስርዓት አላገለግልም” በማለት ዩኒፎርሙን አውልቆ እና መሳሪያውን ለአካባቢው ሰዎች አስረክቦ ከፍኖተሰላም ከተማ መጥፋቱን ምንጮች ገልጸዋል። ወታደሩ መጥፋቱን ተከትሎ ከፍተኛ አሰሳ እየተደረገ ሲሆን፣ በአካባቢው ህዝብ እርዳታ ከአካባቢው ማምለጡ ታውቋል። ከሁለት ሳምንት በፊት አንዲት ሴትን ጨምሮ ስምንት ወታደሮች ከዚሁ ከተማ መጥፋታቸው ይታወቃል።

በብር ሸለቆ አካባቢም እንዲሁ በርካታ ወታደሮች መሳሪያቸውን ሽጠው መጥፋታቸውን ከአካባቢው የደረሰን አስተማማኝ መረጃ ያመለክታል። ለደህንነት ሲባል ስለሰዎቹ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ፍላጎት የሌላቸው ምንጮች፣ ወታደሮቹ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የነጻ አውጪ አባላት ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው ታውቋል።

ይህን ተከትሎ በአካባቢው ባሉ ወታደሮች መካከል አለመተማመኑ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በወታደሮች መካከል ያለው የእርስ በርስ ግንኙነትም በእጅጉ መቀዛቀዙን ገልጸዋል። ወታደሮቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መገናኘት እንደሌለባቸው ትእዛዝ እንደተሰጣቸውም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።