ከሶማሊ ፣ ድሬዳዋና ሌሎች ብሄረሰቦች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌ የተባሉ ሰዎች ወደ ትግራይ በመሄድ ለህወሃት ድጋፋቸውን እንዲገልጹ እየተደረገ ነው

መስከረም ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በቁጥር አነስተኛ ብሄረሰቦችን ይወክላሉ የተባሉ የአገር ሽማግሌዎች እየተመረጡ ወደ መቀሌ በመሄድ በኦሮምያና አማራ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ በማውገዝ ለህወሃት ያላቸውን ድጋፍ ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የክልሉ አስተዳዳሪዎች የአገር ሽማግሌዎችን መርጠው ወደ መቀሌ በመላክ፣ ከአማራ ክልል ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች ድጋፋቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ህወሃት ከአማራ እና ኦሮሞ ህዝብ ውጭ ሌሎች ክልሎች እንደሚደግፉት እንዲሁም የአማራው ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንዳለው ለማስመሰልና የብሄር ግጭት እንዳለ ለማስመሰል የነደፈው እቅድ መሆኑን የዜናው ምንጮች ገልጸዋል።

ከድሬዳዋ ከተማ ብቻ 16 የአገር ሽማግሌ የተባሉ ሰዎች ከትናንት በስቲያ ጉዞ የጀመሩ ሲሆን፣ ከተለያዩ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በጉዞ ላይ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ከደቡብ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው ብቻ ሲፈናቀሉ  ሌሎች ብሄረሰቦች ድርጊቱን አውግዘው አያውቁም። የሶማሊ ክልል ነፍጠኛውና ጠባቦች በትግራይ ህዝብ ላይ የወሰዱትን እርምጃ እናወግዛለን በማለት በክልሉ መሪ ግፊት ሰላማዊ ሰልፍ ማዘጋጀቱንና ክልሉም 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል። ከየክልሉ የተውጣጡት አገር ሽማግሌዎችም ለህወሃት ያላቸውን ታማኝነት ከመግለጽ በተጨማሪ  ከአማራ ክልል ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች ማቋቋሚያ የሚሆን ገንዘብ እንደሚለግሱ ይጠበቃል።