መስከረም ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት ስታደርግ ነበር በሚል በመንግስት የደህንነት ሃይሎች ከመንገድ ላይ ታፍኖ የተወሰደውና በሃሰት የሽብር ክስ ተከሶ ከዓመት ከመንፈቅ በላይ በእስር ሲንገላታ የቆየው አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ ለሕይወቱ አስጊ በሆነ ጽኑ ሕመም ላይ መሆኑ ታውቋል።
በእነ ከድር መሀመድ የክስ መዝገብ በሽብር ክስ የተከሰሰው ጋዜጠኛ ዳርሰማ ከቂሊንጦ የእሳት አደጋ ቢተርፍም በአሁኑ ወቅት ግን መተንፈስ እማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ሆስፒታል እንዲታከም መደረጉን የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ለቤተሰቡ ቢናገሩም የጤንነቱ ሁኔታ ውጪ ወጥቶ ካልታከመ ለሕይወቱ እንደሚያሰጋው ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ በቢላል ራዲዬ እና አፍሪካ ቲቪን ጨምሮ በተለያዩ መገኛኛ ብዙሃን ያገለገለ አንጋፋ ጋዜጠኛ መሆኑ ይታወቃል።