ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)
የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአንድ የቻይና ኩባንያ ለልማት ሊሰጥ ካሰበው ቦታ ላይ እንዲነሱ ጥያቄ የቀረበላቸው በርካታ አርሶ አደሮች ሊሰጣቸው የታቀደው ተለዋጭ ቦታ ለኑሮ ምቹ አይደለም በማለት ተቃውሞን አቀረቡ።
የከተማዋ አስተዳደር ሁአጂየን ለተሰኘው ኩባንያ በተለይም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለቆዳ ኢንዱስትሪ ፓርት ግንባታ 164 ሄክታር መሬት ባለፈው አመት ማስረከቡ ይታወሳል።
የከተማዋ አስተዳደር አዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የያዘውን እቅድ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ዙሪያ መሬትን የተጠየቁ የውጭ ባለሃብቶች ከከተማዋ ዳርቻ ቦታ እየተሰጣቸው መሆኑ ይነገራ።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የእርሻ ቦታዎችን ለውጭ ባለሃብቶች ለመስጠት የያዘውን ዕቅድ መሰረዙ ይታወሳል።
ይሁንና የዕቅዱ አለመሳካትን ምክንያት በማድረግ አስተዳደሩ በአዲስ አበባ ዳርቻ ባሉ ቦታዎች ቃል ለገባው የመሬት አቅርቦት ምላሽን ለመስጠት ጥረት እያደረገ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይገልጻሉ።
ከሶስት ወር በፊት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደ ዘመቻ ግጭት ተቀስቅሶ ከ10 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረሱ ሄደት በተያዘው አመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በቅርቡ ባካሄደው የካቢኔ ልዩ ጉባዔ ውሳኔን አስተላልፏል።
በኦሮሚያ ክልል ከወራት በፊት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ነዋሪዎች አርሶ አደሮችን ያለ አግባብ ከይዞታቸው የማፈናቀሉ ድርጊት እንዲቆምና የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥያቄን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የስብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይኸው ህዝባዊ ተቃውሞ አለም አቀፍ ትኩረት ማግኘቱን ተከትሎ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ግድያውን በመኮነን ድርጊቱ በአለም አቀፉ ገለልተኛ ቡድን አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ጥሪን አቅርበዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ለቀረበው ጥያቄ ተባባሪ እንደማይሆን በመግለጽ የራሱን ማጣራት እንደሚያካሄድ ምላሽን ቢሰጥም፣ ግድያውንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን በየትኛው አካልና መቼ እንደሚያካሄድ ግን የሰጠው መረጃ የለም።