ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው አገራት አንዷ ናት ሲል አንድ አለም አቀፍ ተቋም ይፋ አደረገ

ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ነጻነት የሌለባቸው ሃገራት ተብለው ከተፈረጁ የአለማችን ሃገራት መካከል አንዷ ሆና መገኘቷን አንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም ይፋ አደረገ።

ከ90 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ሃገሪቱ ላለፉት 10 አመታት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን አስመዝግባለች ተብላ ቢነገርላትም፣ ኢኮኖሚያዋ በአብዛኛው ነጻ ያልሆነ ሆኖ በጥናት መገኘቱ በ186 ሃገራት ላይ ያካሄደውን የጥናት ግኝት በህዝብ ያቀረበው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም አስታውቋል።

በነፍስ ወከፍ 250 ካሬ እየተሰጣቸው ለዘመናት ከኖሩበት የእርሻ ቦታ እንዲነሱ የተጠየቁ አርሶ አደሮች የቀረበላቸው ተለዋጭ ቦታ ለኑሮ ምቹ አለመሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ተለዋጭ ቦታው ለልማትም ሆነ ለማህበራዊ ህይወታቸው አመቺ አለመሆኑን በመግለፅ ላይ ያሉት አርሶ አደሮች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊሰጣቸው ባሰበው ምትክ ቦታና ካሳ ላይ ማስተካከያን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ባለፈው ሃምሌ ወር በዚህ ክፍለ ከተማ አካባቢ ህወሃት የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደ ዘመቻ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር መጋጨታቸው ይታወሳል። ሁለት የጸጥታ አባላትና አንድ የክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚ መገደላቸውን እማኞች በወቅቱ ለኢሳት አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ላለፉት 10 አመታት ያህል ጊዜ በአማካኝ አስር በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተመዝግቧል ቢባልም፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ሁሉንም የሃገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች ተጠቃሚ አላደረገም ሲል ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል።

በሃገሪቱ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት ተዘርግቶ ያለው ስርዓት በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሲቪል ማህበረሰብና የመገኛኛ ብዙሃን ቁጥጥር እንዲሁም አፈና እንዲስፋፋ ማድረጉን ዘ-ዴይሊ ሲግናል የተሰኘ መጽሄት የተቋሙን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በኢኮኖሚያዊ ነጻነት ዙሪያ በጥናቱ ከተዳሰሱ 186 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ148ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከሰሃራ በታች አፍሪካ ካሉ ሃገራትም ዝቅተኛ የተባለውን ውጤት በማስመዝገብ በ37ኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች።

በኢትዮጵያ ያለው መጠነ-ሰፊ ሙስና ለኢኮኖሚያዊ ልማቱ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ያወሳው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን ደካማ የሆኑ የህግ ማቀፎች እንዲሁም ማሻሻያ የሚፈልጉ ፖሊሲዎች ትኩረት አለማግኘት በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ነጻነት እንዳይኖር መደረጉ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃም ቢሆን ኣሁን ያላት ኢኮኖሚያዊ ነጻነት አነስተኛ ነው ተብሏል። የጥናቱ ግኝት በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት እንደግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል ታውቋል።

በኢትዮጵያ ተንሰራፍተው ያሉ ኢኮኖሚያው ማነቆዎች ዕልባት ለማስገኘት ሃገሪቱ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባት የ2016 ሪፖርቱን ለንባብ ያበቃው የፋይናንስ ተቋም አሳስቧል።

በባንኮች ዘንድ ነጻ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፉክክር እንዲሁም ፖለቲካዊ መረጋጋት ልዩ ቱኩረት ሊሰጠው ይገባል ያለው ድርጅቱ/የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ያለበት ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ደረጃ ለማሻሻል ዕርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት የፋይናንስ ተቋሙ ጠይቋል።

የአለም ባንክና የሃገሪቱ የልማት አጋሮች ሃገሪቱ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ለመውጣት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።