በኦሮሚያ ክልል መንዲ ከተማ በመስቀል በዓል ዋዜማ አንድ ወጣት ተማሪ ተገደለ

ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ስር በምትገኘው የመንዲ ከተማ በመስቀል በዓል አካባበር ዋዜማ ሰኞ አንድ ወጣት ተማሪ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደሉን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።

ተደጋጋሚ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሄዱባት በቆየችው የመንዲ ከተማ አሁንም ድረስ የጸጥታ ስጋት መኖሩን የተናገሩት ነዋሪዎች የከተማዋ ወጣቶች የደመራ በዓል ዝግጅት እያደረጉ ባለበት ወቅት ወጣቱ በአልሞ ተኳሽ መገደሉን ገልጸዋል።

በወቅቱ ምንም አይነት ተቃውሞ እንዳልነበር ለኢሳት የዜና ወኪኢል ክፍል ያስረዱት የመንዲ ከተማ እማኞች የወጣቱን ግድያ ተከትሎ ነዋሪዎች ተቃውሞ ማሰማት መጀመራቸውን አከለው አስረድተዋል።

የወጣቱ የቀብር ስነስርዓት ማክስኞ የተፈጸመ ሲሆን፣ የመንዲ ከተማ ነዋሪዎች ከመስቃል በዓል አከበባር ሲያደርጉት የነበረው ዝግጅት የሃዘን እና የቁጣ ድባብ እንደታየበት በጉዳዩ ዙሪያ ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ እማኞች አስታውቀዋል።