ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በምደባ ዝውውርን ይፈጸማል ሲሉ ያቀረቡትን የሙስና ቅሬታ ተከትሎ ሲያከናውን የቆየና ንብረትነቱ የማን እንደሆነ ያልታወቀ አንድ ድረ-ገፅ ተዘጋ።
ለኢሳት መረጃን የሰጡ ምንጮች ከትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ወገኖች የተለያዩ የምዝገባ ዘዴዎችን በመጠቀም ከአንድ ተማሪ እስከ 10 ሺ ብር የሚደርስ ክፍያ ሲቀበሉ መሰንበታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ዩኒቨ ኮሌጅ የተሰኘ ድረገጽ ከ3ሺ በላይ ተማሪዎችን ዝውውር አስፈጽማለሁ ብሎ ምዝገባ ማከናወኑን አረጋግጧል።
ይሁንና ሚኒስቴሩ በተጠቀሰው ድረገጽ ላይ ስለሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ቢቆጠበም ድረ-ገጽ ከማክሰኞ ጀምሮ ዝግ መሆኑን አስታውቋል። ድረገጹን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣቱን የገለጸው ይኸው ተቋም ምንም አይነት ክፍያ አለመቀበሉን አስተባብሏል።
በዜና አውታሮች ስማችን መነሳቱ አሳዝኖናል ሲል የድረገፅን መዘጋት ይፋ ያደረገው ዩኒቨኮሌጅ የተማሪዎች ዝውውርን ማከናወን የተከለከለ ስለመሆኑን የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አመልክቷል።
ይሁንና በተያዘው የትምህርት ዘመን ወደ ተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመደቡ ተማሪዎች ከጸጥታ ስጋት ጋር በተገናኘ ዝውውር ለመፈጸም ከትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ሙስና መኖሩን ከኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
የድረገጹን መዘጋት ያስታወቀው ዩኒቨኮሌጅ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች በድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው መሰንበታቸውን አክሎ አስታውቋል።
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለወራት የዘለቀን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከልትሎ ከ20 በሚበልጡ የክልል ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ወደተመደቡበት ቦታ ለመሄድ የጸጥታ ስጋት ያደረባቸው መሆኑን ይገልጻሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ለሁለት ሳምንት የቆየ የመምህራንና የወላጆች ምክክር ሲካሄድ መሰንበቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የውይይት መድረኩ ከተሳታፊዎች ዘንድ ተቃውሞን በማስከተሉ አንድ መግባባት ሳይደርስ መጠናቀቁን ተሳታፊዎች ለኢሳት አስረድተዋል።
ለሁለት ሳምንት እንዲራዘም የተደረገው የዘንድሮው የትምህርት ፕሮግራም በተያዘው ሳምንት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።