መስከረም ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከፍተኛ ቅስቀሳና ማስፈራሪያ በተሰናዳ ሰልፍ በኦሮምያ የሚካሄደውን ተቃውሞ ጠባቦች ያዘጋጁት ነው በማለት ሲወገዝ፣ በአማራ ክልል የሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ደግሞ የትምክተኞች ነው ተብሎአል።
የክልሉ ወኪላችን እንዳለው ከጧቱ 12 ሰአት ላይ የፌደራልና ልዩ ሃይል አባላት በየሰዎች ግቢ ውስጥ በመግባት ህዝቡን ወደ ስብሰባ እንዲወጣ አድርገዋል። ወደ ስብሰባው የሚሄዱ ሰዎች በእጃቸው ምንም ነገር እንዳይዙ የተከለከሉ ሲሆን፣ ወደ ስብሰባው ቦታ ሲደረስ ህዝቡ ጨማውን እያወለቀ ተፈትሿል።
የሌሎች አካባቢ ነዋሪዎች መልእክቱ እንዲደርሳቸው ለማሳየት ሁሉም መፈክሮች በአማርኛ እንዲጻፉ የተደረገ ሲሆን፣ ከመፍክሮች መካከልም “ በባህርዳርና በጎንደርና በኦሮምያ የተካሄደውን በመንግስታችን ላይ የተቃጣውን የተቃውሞ ውዥንብር አጥብቀን እንቃወማለን፣ ትምክህተኞችን ጠባቦችን ና ነፍጠኞችን ከመንግስታችን ጎን በመሆን እንታገላቸዋለን፣ እንዲሁም ግንቦት 7 ና ኦብነግ የሻዕቢያ ተላላኪዎች በመሆናቸው አገር በተላላኪዎች አትፈርስም፣ የትምክህትና ጠባብ ነፍጠኝነት አስተሳሰብና ተግባራት ያፈናቀላቸውን ንጹሃን የትግራይ ተወላጆች መቼውንም ቢሆን ከጎናቸው መቆማችንን እናረጋግጣለን” የሚሉት ይገኙበታል።
በሁለቱ የአገሪቱ ዋና ዋና ክልሎች በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ በማውገዝ የሶማሊ ክልል የመጀመሪያው ሲሆን፣ ድርጊቱ የፖለቲካ ተቃውሞውን ወደ ህዝብ ግጭት ለመቀየር ሆን ተብሎ የተዘጋጀ ነው በማለት የክልሉ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተለይ የኦሮምያና አማራ ክልል ተወላጆች በስብሰባው ላይ ካልተገኙ ከስራ እንደሚባረሩ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን ተቀምተው ከክልሉ እንደሚወጡ የተላለፈው ማስጠንቀቂያ በክልሉ ውስጥ የመኖር ዋስትና እንዳይኖራቸው ማድረጉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰአት በክልሉ ውስጥ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ይጠቀማሉ የተባሉ በርካታ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ውጭ አገራት ለመውጣት ሙከራ አድርገዋል በሚል የተያዙ በርካታ የአማራ ፣ ኦሮምያና የትግራይ ተወላጆች ውጫሌ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ በቅርቡ ከእስር የተፈቱ አንድ ሰው ተናግረዋል።ገንዘባቸውን ከዘረፉ በሁዋላ ከደላላዎች ጋር በመመሳጠር ወደ ሶማሊላንድ እንደሚልኳቸው፣ ገንዘብ መክፈል ካልቻሉ ግን ቶጎ ጫሌ ላይ እንደሚያስሯቸው የአይን ምስክሩ ተናግረዋል። 500 የሚደረሱ እስረኞች ታስረው እንደሚገኙና እርሳቸው ከመግባታቸው በፊት 5 ሰዎች መሞታቸውን እንደተነገራቸው ገልጸዋል ።
በሌላ በኩል ደግሞ በኦጋዴን ነጻነት ግንባርና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል በተደረገ ውጊያ 13 የመከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸውን ግንባሩ አስታውቋል።
በሶማሌ ክልል ቆራሄ እና ሸበሌ አካባቢ በተደረገ ውጊያ 13 የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች መገደላቸውን እና 19 ወታደሮች ደግሞ መቁሰላቸውን ግንባሩ ገልጿል።
የኦጋዴን ነጻነት ግንባር በሶማሊያና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆነችው ሃማሮ ወይም ነጎብ በምትባለው አካባቢ በመስከረም 11ቀን 2009 ዓ.ም በወታደራዊ ኮንቮይ ላይ ባደርሰው ወታደራዊ ጥቃት ሦስት ወታደሮች ሲገደሉ አራቱ ደግሞ ቆስለዋል። በመስከረም 13 ቀን 2009 ዓ.ም በጎሞር ቆራሄ ደግሞ ስድስት ወታደሮች ተገለው ስምንቱ ቁስለኞች ሆነዋል። በተመሳሳይ እለት በመስከረም 13 ቀን 2009 ዓ.ም ሽንሌ ሽበሌ አካባቢ በተደረገ አውደ ውጊያ አራትወታደሮች ተገለው ሰባት መቁሰላቸውን የግንባሩ ወታደራዊ ክንፍ አስታውቋል።
ወቅታዊ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅትም በቀጠናው በሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላትና በኦጋዴን ነጻነት ግንባር ጦር መሃከል ውጊያው ተፋፍሞ ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከልዩ የሚሊሻ ጦር ጋር በጥምረት የኦጋዴን ገጠራማ አካባኢ ነዋሪ የሆኑ መንደሮች ላይ የጭካኔ የጅምላ ግድያቸውን መቀጠላቸውን ግንባሩን ጠቅሶ የኦጋዴን ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል።