ኢሳት (መስከረም 16 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ለውጭ ኩባንያዎች በሊዝ የኢንቨስትመንት መሬት መስጠት ማቋረጡን ቢያሳውቅም፣ አንድ የህንድ የመድሃኒት ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ከ4ሺ ስኩዌር ሜትር በላይ መሬት ለ45 ዓመት በሊዝ መረከቡን ሰኞ ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለውጭ ኩባንያዎች ሲሰጥ የቆየውን ሰፋፊ የእርሻ መሬት በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራን አስከትሏል በማለት መሬት የመስጠቱ ሂደት ከሶስት ወር በፊት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና፣ ባንኩ የተጣለው እገዳ መነሳትን ቢያሳውቅም፣ ኪሊች ድራግ ኢንዲያን የተሰኘ አንድ የህንድ ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ሊያካሄድ ላሰበው የኢንቨስትመንት ስራ 4ሺ 317 ስኩዌር ሜርት መሬት ለ45 አመት ያህል ጊዜ በሊዝ ማግኘቱን ቢዝነስ ስታንዳርድ የተሰኘ ጋዜጣ ኩባንያዋን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ሰፊ መሬቱን ከኢትዮጵያ የገጠር መሬትና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ መረከቡን ያስታወቀው የህንዱ ኩባንያ መሬቱን ለመረከብ ስለፈጸመው ክፍያ ግን የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ኪሊች ድራግ የተሰኘው ኩባንያ ከሱ በተጨማሪ ወደ 80 የሚጠጉ መሬት የማግኘት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ቢያወሳም ኩባንያዎቹ መሬት ያግኙ አያግኙ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
የህንዱ ኩባንያ የተረከበውን ሰፊ መሬት ተከትሎ የኩባንያው የንግድ እንቅስቃሴ ድርሻ በ20 በመቶ አካባቢ እድገትን ማሳየቱን ከኩባንያው ድረ-ገጽ ከሰፈረ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ባለፈው አመት በርካታ የህንድ ኩባንያዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬትን ከተረከቡ በኋላ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመበደር የወሰዱትን ብድር ሳይከፍሉ ከሃገር መኮበለላቸው ይታወሳል።
በዚሁ ድርጊት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ያመነው ልማት ባንክ፣ ኩባንያዎቹ የወሰዱትን ገንዘብ እንዲመልሱ ለማድረግ ክስ እንደሚመሰርት በቅርቡ ይፋ ማድረጉን ዘግበናል።
በኢትዮጵያ ለአመታት ሲካሄድ ቆይቋል የተባለው የመሬት ቅርምት በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ያደረገ ሲሆን፣ መሬታቸውን ለልማት በሚል የተነጠቁ አርሶ አደሮች በቂ ካሳ እንዳልተከፈላቸው ቅሬታን ሲያቀርቡ ቆይቷል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት ከልማት አጋሮች ሲቀበል የነበረውን ድጋፍ ለመሬት ቅርምቱ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ አውሎታል በማለት ምርመራ እንዲካሄድ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይህንኑ አለም አቀፍ ዘመቻ ተከትሎ የሃገሪቱ የልማት አጋር የሆነውና ጥያቄው ሲቀርብለት የነበረው የአለም ባንክ በገለልገኛ ቡድን ምርመራን አካሄዶ የነበረ ሲሆን፣ ቡድኑ በመንግስት በኩል የልማት ድጋፎች ለመሬት ቅርምት ማስፈጸሚያ መዋሉን በማረጋገጥ ሪፖርቱን ባልፈው አመት ይፋ አድርጓል።
የሪፖርቱን ይፋ መደረግ ተከትሎ የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የማስተካከያ ዕርምጃን እንዲወስድ ውሳኔን አስተላልፏል።
በአለም ባንክ በኩል የልማት ድጋፍን ሲሰጥ የቆየው የብሪታኒያ መንግስት በበኩሉ በየአመቱ ሲሰጥ የቆየውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንዲቋረጥ መወሰኑ ይታወሳል።
በተመሳሳይ መልኩ የአውሮፓ ፓርላማ በሃገሪቱ እየተፈጸሙ ይገኛል ያላቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በማውገዝ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ እርምጃን እንዲወስድ ውሳኔን አቅርቦ ይገኛል።