ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ስርዓት አማካይነት እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ፣ ግድያ፣ የጅምላ እስርና ስቃይ የሚያወግዙ ሰልፍች በተለያዩ ሀገራት ከተሞች እንደቀጠለ ነው።

መስከረም ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ስርዓት አማካይነት እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ፣ ግድያ፣ የጅምላ እስርና ስቃይ የሚያወግዙ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለሚደረገው ትግል አጋርነትን የሚገልጹ ሰልፍች እንዲሁም በግፍ ለተሰው ወገኖች የጸሎትና የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት የማዳረጉ ሂደት አሁንም በተለያዩ ሀገራት ከተሞች እንደቀጠለ ነው። ያሳለፍነው ቅዳሜ በጀርመኖቹ የፍራንክፈርትና የቩርዝቡርግ ከተሞችም ሰላማዊ ሰልፍና የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት የተከሄደ ሲሆን ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ ያሰቡትን እቅድ እንዲመረምሩ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ተግባር ሲከናወን ውሏል።