አርበኞች ግንቦት 7 በደርባን የተሳካ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ መስራቱን አስታወቀ

መስከረም ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የድርጅቱ አባላትና አስተባባሪዎች እንደገለጹት በደርባን፣ ጆሃንስበርግ፣ ፕሪቶሪያና ራስተምበርግ ለድርጅቱ ማጠናከሪያ ገቢ ለማሰባሰብ እቅድ የተያዘ ሲሆን፣ የመጀመሪያው በደርባን ከተማ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል። እሁድ መስከረም 15፣ 2009 ዓም በተካሄደው ዝግጅት ላይ ህዝቡ ለድርጅቱ ያሳየው ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር የገለጹት አዘጋጆች፣ በአገራችን እየተፈጸመ ያለው አፈና እና ግድያ እንዲቆም ተሰብሰባው በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገባበት እንዲሁም በደርባን የኢትዮጵያውያን ስብሰባ ታሪክ ያልታየ  ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ የተሰራበት ነበር ሲሉ አክለዋል።

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ የመምህር በቀለ ገርባ፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዴና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ምስል ለጨራታ ቀርቦ በ236 ሺ 400 የደቡብ አፍሪካ ራንድ መሸጡን አስተባባሪዎች ተናግረዋል። በዝግጅቱ ላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የአመራር አባል የሆኑት አቶ ብዙነህ ጽጌና አቶ ንአምን ዘለቀ በስካይፕ መልዕክት አስተላልፈዋል።