በፍኖተሰላም 8 ወታደሮች እስከ እነ ሙሉ ትጥቃቸው በመጥፋታቸው እየተፈለጉ ነው

መስከረም ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ላይ ለጥበቃ የተሰማሩት ወታደሮች መጥፋታቸው ታውቋል። አካባቢው በአጋዚ ወታደሮች እየታሰሰ ሲሆን እስካሁን ድረስ ያሉበት አልታወቀም። ከጠፉት 8 ወታደሮች መካከል አንዷ ሴት ናት።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል አዲስ የአድማ በታኞችን ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቷል።

ክልሉ ባጋጠመው ከፍተኛ የአድማ በታኝ ሃይል የተነሳ አዲስ ቅጥር ለመፈጸም ማስታወቂያ አውጥቷል። ማስታወቂያው ከመስከረም 12 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11 ምዝገባ እንደሚጀመር የሚያትት ሲሆን ለህገመንግስቱ ታማኝና ተገዢ የሆነ የሚል መስፈርትም ተቀምጧል።

በክልሉ ከሚታየው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጋር በተያያዘ ከየወረዳዎች የተውጣጡ ልዩ የሚሊሺ አባላት “ በቃን” እያሉ ወደ መጡበት አካባቢ መመለስ ጀምረዋል፡ በወር እስከ 1 ሺ ብር ደሞዝ እንደሚከፈላቸው ቃል የተገባላቸው እነዚሁ ሚሊሺዎች ለአንድ ወር ያክል የተባሉትን ትእዛዝ ሲፈጽሙ ከቆዩ በሁዋላ፣ በመጨረሻ የተሰጣቸው ገንዘብ ከ500 ብር ያልበለጠ ሆኖ በማግኘታቸው ብዙዎች ብስጭታቸውን እየገለጹ ተመልሰው ወደ ቀያቸው እየሄዱ ነው።