ኢሳት (መስከረም 12 ፥ 2009)
በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ሃሙስ ለአራተኛ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በመንግስት የጸጥታ ህያሎች ይፈጸማል ያሉትን ግድያና የጅምላ እስር በማውገዝ ሰኞ የስራ ማቆም አድማ መጀመሪቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይኸው ህዝባዊ ተቃውሞ በሁለቱ ከተሞች መቀጠሉን ለመረዳት ተችሏል።
የመንግስት ባለስልጣናት የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ስራቸውን እንዲጀምሩ በማስገደድ ላይ ቢሆኑም የንግድ ባለቤቶቹ ስራ ላለመጀመር መወሰናቸው ታውቋል።
ይሁንና በጎንደር ከተማ የኢሳት ቃጠሎ ለማድረስ እየተደረገ ያለው ሙከራ በነዋሪዎች ዘንድ ተጨማሪ ቁጣን እየቀሰቀሰ እንደሚከገኝ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በከተማዋ የእሳት ቃጠሎን ለማድረስ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩትና በቁጥጥር ስር የዋሉት አምስቱ ግለሰቦች ድርጊቱን ለመፈጸም የሚረዳ ቤንዚን እና ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዘው እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።