በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረገው ምክክርና ስልጠና ከመምህራን ዘንድ ተቃውሞ ገጠመው

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመካሄድ ላይ ያለው ምክክርና ስልጠና ከመምህራን ዘንድ ተቃውሞ እየገጠመው መሆኑ ታውቋል።

መምህራኑ በአወያዮች ከቀረበው አጀንዳ በተጨማሪ ወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳዮች በመወያያነት እንዲነሱ ጥያቄን ቢያቀርቡም ከአወያዮች ተቀባይነት አለማግኘቱን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ መምህራን ገልጸዋል።

መምህራኑ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ተከትሎም መምህራኑ በመድረኩ ምንም አይነት አስተያየትና ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው የመንግስት ተወካዮች ብቻ ንግግር አቅራቢ ሆነው መቀጠላቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የማይሆኑ መምህራን ከስራቸው ይሰናበታሉ ሲሉ የማስፈራሪያ ማሳሰቢያ በማሰራጨት ላይ መሆኑን መምህራኑ ለኢሳት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የትምህርት ሚኒስቴር መስከረም 3 መጀመር የነበረበትን ትምህርት መስከረም 18 ፥ 2009 ዓም እንዲራዘም በማድረግ መምህራንን እና ወላጆችን ከትምህርት ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ዙሪያ ለ14 ቀናት የሚቆይ ስልጠናን እየሰጠ ይገኛል።

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በትምህርት ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራሉ ተብሎ በመሰጋቱ ትምህርት ሚኒስቴር ስልጠናውን ለማዘጋጀት መገደዱን መምህራን ይገልጻሉ።

ከመምህራን ጋር እየተካሄደ ያለው ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጣዩ ሳምንት ተመሳሳይ መድረክ ከወላጆች ጋር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ወላጆች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በሚመደቡ ተማሪዎች ደህንነት ዙሪያ ስጋት እየተሰማቸው መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው።