ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)
በተለያዩ ክልሎች በመካሄድ ላይ ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምክክር ጋር በተያያዘ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ለምክክሩ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም ተብለው ከሃላፊነታቸው ተነሱ።
ከቀናት በፊት ለአመታት ካገለገሉበት ሃላፊነት የተነሱን ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው፣ የትምህርት ሚኒስቴር ለስንብቱ የሰጣቸው ምክንያት ትክክለኛ አለመሆኑንና ካህገር አቀፍ ስልጠናና ምክክር ተሳታፊ እንደነበሩ ምላሽን ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞ ለስልጠናው ቅድመ ዝግጅት ትብብር ካለማድረጋቸው በተጨማሪ፣ የትምህርት ሚኒስቴርን ፈቃድ ሳይጠይቁ ወደ ውጭ ሃገር መሄዳቸውን ለውሳኔው መንስዔ መሆኑን በትምህር ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በሃገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ቅድመ ዝግጅት ወቅት ተሳታፊ እንደነበሩ ምላሽን የሰጡት የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት በወቅቱ ከትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንን ጋር መገናኘታቸው አስረድተዋል።
ይሁንና የትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት በቅድመ-ዝግጅቱ ወቅት ተባባሪ አልነበሩም የሚል ምክንያት በመስጠት በምትካቸው በማስተማር ስራ ላይ የሚገኙትን አቶ አያናው ባሪሶን እንደሾመ ታውቋል።
ላለፉት አምስት አመታት የሃዋሳ ዩኒቨርስቲን በፕሬዚደንትነት ሲያገለግሎ የነበሩት ፕሮፌሰር ዮሴፍ የደረሳቸውን የስንብት ደብዳቤ ተከትሎ ለትምህርት ሚኒስትሩ የጹሁፍ ምላሽ ማቅረባቸው ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ፕሬዚደንቱ ለሃላፊዎች ስለሰጡት ምላሽ ዝርዝርን መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ባለፈው አመት የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ስለሺ ኮሬ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተገኛኘ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚታወስ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ለበርካታ አመታት በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እንዲሁም ዶ/ር መረራ ጉዲና መሰናበታቸው ይታወቃል።