ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በመፈጸም ላይ ያሉ ግድያዎችን በመቃወም ሰኞ በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ማክሰኞ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ታውቋል።
በየከተሞቹ ያሉ የንግድ ቢሮዎች የስራ ማቆም አድማ የጀመሩ ድርጅቶች አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ግፊትን በማድረግ ላይ ቢሆንም የንግድ ተቋማቱ ባለቤቶችና ባለንብረቶች ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
የትራንስፖርት እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለሁለተኛ ቀን ሙሉ ለሙሉ አገልግሎትን አቋርጠው የሚገኙ ሲሆን፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥራቸው በአግባቡ ያልታወቀ ሰዎችን እንዳሰሩም ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች አመልክተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በባህርዳት ከተማ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ለሁለተኛ ቀን የቀጠሉትን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከተማዋ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በሁለቱ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለው የስራ ማቆም አድማ የዳሸን ቢራ ፋብሪካን ጨምሮ በበርካታ የመንግስታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ታውቋል።
በሁለቱ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለው የስራ ማቆም አድማ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለው የሃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲሁም ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ በመጠየቅ ላይ ናቸው።