በባህር ዳር ሆምላንድ ሆቴል ነጋዴዎችን ያሳተፈ ስብሰባ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው

ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)

በባህር ዳርና በጎንደር ሰኞ ዕለት የተጀመረው አድማ በቀጠለበት ወቅት በባህር ዳር ሆምላንድ ሆቴል የተጠራው ስብሰባ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የኢሳት ምንጮች ገለጹ። ም/ጠ/ም/ር እና የብአዴን ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን በመሩት በዚሁ ስብሰባ ላይ የተጠሩት ነጋዴዎችና የአካባቢው ታዋቂ ሰዎች ሃገር የመምራት ብቃት ስለሌላችሁ ስልጣን ልቀቁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰብሳቢዎቹን “አሁን እናንተ አማራ ናችሁ ወይ?” በማለት አስተያየት የሰጡ ተሰብሳቢ አማራ ከሆናችሁ አማራው ሲገደል ለምን አይሰማችሁም በማለት ጠይቀው እባካችሁ አቅም ላላቸው ስልጣናችሁን ልቀቁ ሲሉ የተሰብሳቢውን የጭብጨባ ድጋፍ አግኝተዋል። “መፍትሄ እንፈልግ ብላችሁ እዚህ ሰብስባችሁን ወንድሞቻችንን እየገደላችሁ ሱቆቻችንን እያሸጋችሁ እንዴት እንመናችሁ?” በሚል ለተነሳው ተቃውሞ ተሰብሳቢው ድጋፉን መስጠቱንና የኢሳት ምንጮች ከስፍራው አድርሰዋል።

የአማራ ክልልን ወደ ሱዳን መውጫ በመንሳት፣ የራስ ዳሸንን ተራራ የትግራይ ክልል ነው በሚል በመማሪያ መጽሃፍ ላይ መታተሙን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ አቶ ደመቀ መኮንን የሰጡት ምላሽ ተሰብሳቢውን ፈገግ ያስደረገ እንደነበርም ተመልክቷል። ካርታው ሆን ተብሎ አይደለም የተሰራው በስህተት ነው ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን፣ ካርታውን የሰራውም የትግራይ ሰው ሳይሆን፣ የጋሙ ጎፋ ሰው ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም በተሰብሳቢው በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱም ተመልክቷል።