መንግስት በኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ላይ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ መሆኑ ተነገረ

ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)

በደቡብ ክልል የሰገን ህዝቦች ዞን ስር የሚገኙ የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ሰሞኑን በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች የተከፈተባቸው ዘመቻ መቀጠሉንና ሰኞ በትንሹ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ለኢሳት አስታወቁ።

የህዝብ ተወካይ ኮሚቴ አባላትን ለመያዝ በሚል ሰኞ በዞኑ ስር በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በተፈጸመ ጥቃቅን ህይወቱ ያለፈው የአንድ ነዋሪ፣ አስከሬኑ ከአንድ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋም አጠገብ ተጥሎ መገኘቱን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

ግድያ ከተፈጸመበት ግለሰብ በተጨማሪ ሁለት ነዋሪዎች በተፈጸመባቸው ድብደባ የተነሳ አርባ ምንጭ ከተማ ለአስቸኳይ ህክምና መወሰዳቸው ታውቋል።

በዞኑ የተለያዩ ቀበሌዎች ሰፍረው የሚገኙ የመከላከያ፣ የፌዴራልና የክልሉ ልዩ ሃይሎች የህዝብ ተወካይ ኮሚቴ አባላትን ለመያዝ በሚል የቤት ለቤት ፍተሻ እያካሄዱ መሆኑንና የግለሰቦችን ንብረት መዝረፍ እንደጀመሩ ከኢሳት ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በቅርቡ በዞኑ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎ ወደ 50 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን የሚናገሩ ነዋሪዎች 14 አስከሬን አሁንም ድረስ በፖሊስ እጅ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዞኑ በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ውጥረቱ ተባብሶ እንደሚገኝ እማኝነታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የቤት ለቤት ፍተሻን በማካሄድ ላይ ያሉ የጸጥታ ሃይሎች ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶችን እየወሰዱባቸው እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ከሁለት አመት በፊት በወረዳ አልያም በዞን እንዲደራጁ ጥያቄን ቢያቀርቡም ያቀረቡት ጥያቄ በደቡብ ክልልና በፌዴራል መንግስት በኩል ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

ይሁንና ወደ ግማሽ ሚሊዮን እንደሚደርሱ የሚነገርላቸው የብሄረሰቡ አባላት ጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚያገኝ ጥያቄን ዳግም በማቅረብ እንደሆኑ ታውቋል።

የብሄረሰቡ አባላት ያቀረቡትን ጥያቄ በማስተባበር ላይ ናቸው የተባሉ ነዋሪዎችን ለመያዝ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሁለት ወረዳዎች ውስጥ የሃይል እርምጃን እየወሰዱ እንደሆነ እማኞች ለዜና ክፍላችን አክለው ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በዞኑ ስር በሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሆን ተብሎ የመኖሪያ ቤታቸውን የማቃጠል ድርጊት እንደተፈጸመ እማኞች ለኢሳት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚሁ አደጋ ወደ 12ሺ የሚደርሱ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግስት የገለጸ ሲሆን፣ ድርጊቱን ግን በህዝብ ተወካይ ኮሚቴ አባላትና በነዋሪው በኩል በተፈጠረ አለመግባባት የተከሰተ በመሆኑ ነው አሰተባብሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በጸጥታ ሃይሎች እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ህዝቡ ያነሳውን ጥያቄ ሌላ መልክ ለማስያዝ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።