ከ1 ሺ 500 በላይ ወጣቶች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ጫካ ውስጥ ታስረው ስቃይ እየደረሰባቸው ነው ተባለ

መስከረም ፲ (አሥር) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል የተካሄዱ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን ተከትሎ ከታሰሩት ከ1 ሺ700 እስከ 2 ሺ የሚደረሱ ወጣቶች ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ታስረው ቀኑን ሙሉ ድንጋይ በመፍለጥ እየተቀጡ መሆኑን፣ ብዙዎች በበሽታ፣ በርሃብ እና በህመም ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን፣ በእስር ቤቱ ታስሮ ያመለጠ አንድ የቀድሞ ወታደር ለኢሳት ገልጿል።

በጠባቂ ጓደኞቹ ድጋፍ ያመለጠው ይህ የቀድሞ ወታደር፣ በወጣቶች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ከተመለከተ በሁዋላ፣ ስርዓቱን ማገልገሉ በእጅጉ ቆጭቶታል።

ጠባቂ ወታደሮች ስለ እስረኞቹ ምንም እንደማያውቁ ፣ እርስ በርስ እንደማይነጋጋሩና ከውጭ ካለው ማህበረሰብ ጋር በፈጽሙ እንደማይገናኙ የገለጸው ወጣቱ፣ በውትድርና ውስጥ እያለ በሚያውቃቸው ሰዎች እርዳታ መጥፋቱንና ህይወቱን ማትረፉን ተናግሯል።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ  በመካሄድ ላይ ባለው የመምህራን ውይይት ወቅት የታሰሩት ወጣቶች እጣ ፋንታ እንዲነገራቸው መምህራን ሲያቀርቡ፣ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው የሚል ምላሽ በመሰጠቱ መምህራን ተቃውሞአቸውን ገልጸው ነበር።

እነዚህን እስረኞች ከሞት ለመታገድ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊረባረብ እንደሚገባ ወጣቱ ገልጿል።