በአውስትራልያ ኩዊንስ ላንድ ግዛት ብሪዝቤን ከተማ ዛሬ በህወሃት መራሹ መንግስት ሂወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን የማሰብና ለሌሎችም ወገኖቻቸው አጋርነትን የመገልጸ ስነስርዓት ተከናወነ።

መስከረም ፲ (አሥር) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በኩዊንስ ላንድ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ባዘጋጀው በዚህ ዝግጅት ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን የታደሙ ሲሆን የደብረ ጸሃይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ካህንና አስተዳዳሪ ቄስ መንግስቱ ሃይሉ በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ቡራኬና ትምህርት የሰጡ ሲሆን ለዕለቱ የተዘጋጀውንም ሻማ ለኩሰዋል። ልዩነቶቻችንን አቻችለን በጋራ በመቆም ሃገራችንንና ወገኖቻችንን መታደግ ይገባል ሲሉ ያሳሰቡት ቄስ መንግስቱ በህብረትና በጋራ መቆም ግዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ለታዳሚው አበክረው ገልጸዋል በኩዊንስ ላንድ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ፕሬኧደንት ኢንጂነር አንተነህ ሽፈራው በበኩሉ ወደኋላ በመሄድ ኢትዮጵያ በታሪኳ የገጠሟትን ታሪካዊ ተግዳሮቶችና ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አጭር ዳሰሳ ለተሰብሳቢው አቅርቧል። ኢንጂነር አንተነህ የዚህ ዝግጅት መዘጋጀትን አስመልክቶ ሲገልጽ ኮሚዩኒቲው በየዓመቱ የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት አስመልክቶ ያደርገው የነበረው የሙዚቃ ድግስ ዘንድሮ ሃገራችን ውስጥ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው አሳዛኝ ጭፍጨፋ የተነሳ መሰረዙና እንዲ ባለ መልኩ ለማሳለፍ መወሰኑን አስረድቷል። አክሎም ጣልያን ኢትዮጵያን ስትወር የተከተለቻቸውን ስትራቴጂዎችን በማውሳት ከህወሃት መንግስት ጋር ያለውን ተመሳሳይነት ለተሰብሳቢው አስረድቷል። ይህንንም ዘግናኝ የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ለመበጣጠስ የሚቻለው በጋራ ቆሞ መታገል ሲቻል መሆኑን ገልጾ ስለተሰዉት ወገኖቻችን የተሰማውን ሃዘን በቁዊንስ ላንድ ኮሚዩኒቲ ስም ገልጾ ላዘኑ ሁሉ መጽናናትን ተመኝቷል።

ታዳሚው በዝግጅቱ ላይ ንፍሮ ቀቅሎ  በማቅረብና ጥቁር በመልበስ ካዘኑት ወገኖቻቸው ጎን መቆማቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በወቅታዊው የሃገራችን ጉዳይ ላይም ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል። በቀጣይ ሃገር ቤት በሚደረገው ትግል ላይ ማህበረሰቡ ሊኖረን ስለሚችለው ሚናም ሃሳብ ተንሸራሽሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸውን የሚደረገውን ህዝባዊ ትግል በመደገፍና አገዛዙ የሚወስደውን እርምጃ በማውገዝ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ጥያቄያቸውንም ለውጭ ጉዳይ መስሪያቤቱ አቅርበዋል። በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ በእስራኤል እንዲሁም በፈረንሳይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸውን የሚፈጸመውን ግፍ በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፎችን ማድረጋቸው ይታወቃል።