ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ታዋቂዋ ኢኮኖሚስት ዳምቢሳ ሞዮ “የምእራባዊያን እርዳታ ማእከል የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ህልቆ መሳፍርት የውጭ እርዳታ ብታገኝም፣ አገሪቱ ግን አሁንም ከድህነት አልወጣችም” አሉ
የ”ዴድ ኤንድ”ና የ “ሀው ዘ ዌስት ወዝ ሎስት” የሚሉ መጽሀፎችን የጻፉት ታዋቂዋ ኢኮኖሚስት ደምቢሳ ሞዮ ፣ “የኢትዮጵያ መንግስት የእርዳታ ለጋሾች ወዳጅ በመሆን በቡድን ስምንት አገሮች ስብሰባ ሳይቀር
ቢገኝም፣ በኢትዮጵያ ግን አሁንም ድህነት ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ” ገልጠዋል
“በጋና፣ በኬንያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሞባይል ቴክኖሎጂ መረጃዎችን በመለዋወጥ ለገበያ ፍሰት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የገለጡት ኢኮኖሚስቷ፣ የሞባይል ፍሰቱ በአፍሪካ 30 በመቶ ሲደርስ የምእራባዊያን ቅምጥል አገር በሆነችው ኢትዮጵያ 2 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
በአውሮፓ የሞባይል ስርጭት 100 በመቶ መድረሱን የሚናገሩት ሞዮ፣ በኢትዮጵያ የሞባይል ቴክኖሎጂ ለመንግስት ገቢ የሚያስገኝ እንዲሁም የህዝቡን ህይወት በመለወጥ በኩል አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ መንግስት ግን ሆን ብሎ ገበያውን እንደዘጋው አጋልጠዋል።
በአለም ላይ አንድም አገር በእርዳታ አለማደጉን የሚናገሩት ሞዮ፣ “በአፍሪካ የፖለቲካ ተቋማት ፣ ዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳዳር ሊገነቡ የሚችሉት፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በብዛት ሲፈጠሩ ብቻ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።
“የአፍሪካ መሪዎች ለእራሳቸው ህዝብ ፍላጎት ጆሮ የሚሰጡ ባለመሆናቸው ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ አለመቻሉን ኢትዮጵያን በምሳሌ በማንሳት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሞባይል ስርጭት እንዳይስፋፋ የሚከላከለው የፖለቲካ ስልጣኑን ለማራዘም ሲል መሆኑን ብዙዎች ይገልጣሉ።
በምርጫ 97 ወቅት የኤስ ኤም ኤስ መልእክቶች በሞባይል እንዳይሰራጩ መንግስት አግዶ እንደነበር ይታወቃል። የኢትዮጵያ ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያ ያነሰ የኢንተርኔትና የስልክ ስርጭት እንዳላት ይታወቃል።