ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት እየፈጸመ ያለው ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በእስራዔል በሚኖሩ ቤተ-እስራዔላውያንንና ኢትዮጵያውያን ዘንድ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ዘጄሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ መክሰኞ ዘገበ።
በዚሁ የመንግስት ድርጊት ቁጣ ያደረባቸው ከ250 በላይ ቤተ እስራዔላውያን ቴላቪቭ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ጋዜጣው ማክሰኞ ለንባብ ባበቃው እትሙ አስፍሯል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የፖለቲካና የልማት አጋር በመሆኗ ሰልፈኞቹ የሃገሪቱ መንግስት ጫናን እንዲያደርግ ለመጠየቅ ሰልፋቸውን በኤምባሲው ፊት ለፊት ሲያካሄዱ ማርፈዳቸውን ዘጄሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል።
በመንግስት በመፈጸም ላይ ያሉ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለቤተ-እስራዔላዊያኑ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ያወሳው ጋዜጣው፣ ለወራት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት ወደ 140 ሺ የሚጠጉ ቤተ-እስራዔላውያን በእስራዔል እንደሚኖሩ ያመለከተው ጋዜጣው ተቃውሞን ሲያሰሙ ያረፈዱት ሰልፈኞች የአሜሪካን መንግስት በመፈጸም ላይ ያሉ ሰላማዊ ሰዎችን ግድያ በማገዝ እርምጃን እንዲወስድ ማሳሰባቸውን አስነብቧል።
እንዳላማው ሃይሌ የተባለ እና በሰላማዊ ሰልፉ የታደመ ቤተ-እስራዔላዊ አሜሪካ የኢትዮጵያንን ግድያ ማውገዝ ይኖርባታል፥ የኢትዮጵያም ጉዳይ ያሳስበኛል ሲል ለጋዜጣው ገልጿል።
በኢትዮጵያ በተለይ በአማራ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም በደቡብ ክልል በኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ግድያዎችን በማውገዝ ሰኞ ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና የተለያዩ ግዛቶች የሆነ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመሳሳይ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
በ10 አመት ውስጥ ታላቁ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ እርጅማን እንዲወስድ አሳስቧል።
በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን የተገኙበት ይኸው ሰላማዊ ሰልፍ የታቀደለትን አላማ ያሳካ እንደነበር ሰልፉን ያዘጋጁትን አካላት ለኢሳት ገልጸዋል።
መቀመጫቸውን በዚህ በአሜሪካ ያደረጉ ወደ 25 የሚጠጉ የፖለቲካ፣ የሲቪክና የሃይማኖት ተቋማት ሰላማዊ ሰልፉን ማዘጋጀታቸው ይታወሳል።