መስከረም ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን የጠየቁ ዜጎች የኦሮሚያ እና አማራ ብሔረሰቦችን ጨምሮ በተለያዩ የአገርቱ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኦጋዴን ነጻነት ግንባር አስታውሷል። በዜጎች መሃከል የእርስበርስ እልቂት እንዲፈጠር ሆን ተብሎ በገዥው ፓርቲ እየተሰራ ሲሆን፣ በተለይ በሶማሊያና ኦሮሞ ብሔረሰቦች መሃከል ግጭት በመፍጠር ሰላማዊ ዜጎች ተገለዋል፣ ተሰደዋል፣ በግፍ ታስረዋል።
በሶማሊያና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ወሰኖች አቅራቢያ ነፍጥ የታጠቁ የልዩ ሃይል ጦር አባላት በዜጎች ላይ እልቂት እየፈጸሙ ነው። በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ የልዩ ጦር አባላት በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። የሶማሌ ክልል ጦር አባላት ከክልሉ አልፈው በሰሜን ሶማሊያ፣ ጅቡቲ ውስጥ በሚኖሩ የአማራና የኦሮሞ ብሔረሰብ ሰራተኞች ላይ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ ሰቆቃዎችን እያደርሱባቸው ሲሆን፣ ይህም በመንግስት የተቀነባበረ ሴራ ለቀጠናው ስጋት መፍጠሩን የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ገልጿል።
በኦጋዴን አንዳንድ ከተሞች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞና አማራ ብሔር ተወላጆች በመንግስት ወታደሮች እና የአካባቢ ሚኒሻዎች ተገለዋል፣ ከሕግ አግባብ ውጪ በጅምላ ታሰረዋል፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት አገራት ተሰደው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ድሃ የቀን ሰራተኞች ጭምር በህወሃት/ኢህአዴግ የተቀነባበረ ሴራ ከአገራቸው ውጪም ሰቆቃ እየተፈፀመባናቸው መሆኑን ግንባሩ አስታውቋል። ይህንን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማውገዝ የተቃወሙ የሶማሌ የሃይማኖት አባቶች፣ አዛውንቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በፀጥታ ኃይሎች ተደብድበዋል። ይህም ገዢው ፓርቲ ሆን ብሎ በሶማሌ ብሄረሰብና በሌላው የኢትዮጵያ ብሔሮች መሃከል ግጭትና ጥላቻ እንዲፈጠር በማድረግ በኅብረተሰቦች መሃከል ኅብረት እንዳይኖር ለማድረግ መሞከሩን ያመላክታል።
“የኦጋዴን ሕዝብ ይህን የከፋፍለህ ግዛ ሴራን የሚያውቀው ሲሆን ምንጊዜም በብሔራቸው ይሁን በእምነታቸው መብታቸውን ካጡና ከተጨቆኑ ዜጎቻችን ጎን ይሰለፋል ። የኢትዮጵያ መንግስት ከ2007 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ የጦር ወንጀል መፈጸሙን ቀጥሎበታል። በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገለዋል፣ ተፈናቅለዋል አድራሻቸው የማይታወቁም የክልሉ ነዋሪዎች አሉ። ይህ ሁሉ በደል እየተፈጸመ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኦጋዴን ነጻነት ግንባር የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮችና የአካባቢው ሚኒሻዎች መጪውን ዘመን በማሰብ ከእኩይ ድርጊታቸው ታቅበው ከሕዝባቸው ጎን እንዲሰለፉ ጥሪውን ያቀርባል።” ብሎአል።
ግንባሩ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራውን አንባገነኑን ስርዓት መደገፉን እንዲያቆምም ጠይቋል። የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ይህንን የተዳከመ ገዥ አካል ድጋፍ እንዳያደርጉ ማሳሰብ ጀምረዋል። ግንባሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የሚያሳትፍ ስርዓት ለመመስረት በሚደረገው ትግል ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደሚሰራና ለለውጡ ዜጎች በጋር እንዲነሱ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።