ኢሳት (መስከረም 6 ፥ 2008)
ሰሞኑን በደቡብ ክልል በሚገኘው የሰገን ህዝቦች ዞን ኮንሶ ወረዳ በተቀሰቀሰው ግጭት ወደ 12ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግስት አርብ አስታወቀ።
የዞን ነዋሪዎች ሃሙስ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎኦች በኮንሶ ብሄረሰብ የተነሳውን አስተዳደራዊ ጥያቄ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ በአካባቢው ሆን ተብሎ ግጭትን እንዲቀሰቅስ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚሁ የጸጥታ ሃይሎች ድርጊት በርካታ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውንና ለዘመናት በስፍራው የኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዚሁ ግጭት ዙሪያ ምላሽን የሰጠው የክልሉ መንግስት ወደ 12ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ድርጊቱም አስተዳደራዊ ጥያቄ እንዲነሳ ባደረጉ አባላትና በነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ አመልክቷል።
ይሁንና የዞኑ ነዋሪዎች ውጥረትን አንግሶ የሚገኘው ይኸው ግጭት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንደሆነ ለኢሳት ተናግረዋል።
የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ በወረዳ አሊያም በዞን ስር እንዲደራጁ ጥያቄን ቢያቀርቡም የክልሉ መንግስት ምላሽ መንፈጉን ለመረዳት ተችሏል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ለምክር ቤቱ ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር በማውሳት ጥያቄውን የሚመለሰው አስፈጻሚ እንጁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አይደለም ሲሉ ለመንግስት መገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በዞኑ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የጸጥታ ሃይል እንዲሰራማ መደረጉን ቢገለጽም በአካባቢው በሰዎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች በበኩላቸው ተማሪዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመርዳት ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
ያቀረቡት አስተዳደራዊ ጥያቄ ህጋዊ መሰረት ያለው በመሆኑ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አክለው ገልጸዋል።