ኢሳት (መስከረም 5 ፥ 2009)
በአዲስ አበበ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ት/ቤቶች ከረቡዕ ጀምሮ መካሄድ የጀመረው የመምህራን ውይይይት ከአስተማሪዎች በኩል ተቃውሞ እንዳጋጠመው መምህራት ለኢሳት አስታወቁ።
ለዚህ ሃገር አቀፍ ውይይት እንዲሳተፉ ጥሪ የቀረበላቸው መምህራን መንግስት ወዳቀረበው የመወያያ አጀንዳ ከመገባቱ በፊት መምህራንን የቅድመ ሁኔታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተሳታፊ መምህራን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ረቡዕ የተጀመረው ይኸው የመምህራን ውይይት በቀረበው የትምህርት ስርዓት ላይ ለመወያየት አጀንዳ ቢኖረውም መምህራን በሃገሪቱ ስላሉ ተቃውሞዎችና ውጥረቶች ጥልቅ ውይይት እንዲካሄድ መጠየቃቸው ታውቋል።
ይሁንና አወያይ ተወካዮቹ ከመምህራኑ ለቀረበው ጥያቄ አግባብ ያለው ምላሽ ባለመስጠታቸው ውይይቱ አለመግባበት መፍጠሩን የውይይቱ ተሳታፊ መምህራን አስረድተዋል።
መምህራን ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ተከትሎ ተሳታፊ መምህራን በሁለተኛ ቀን በመድረኩ ከመሳተፍ ውጭ ድምፀ-ተአቅቦ ለማድረግ ውሳኔ ማድረጋቸውን መምህራኑ ከኢሳትጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስት ከመምህራን ወላጆች ጋር ምክክርን ለማካሄድ እንዳስገደደው እማኞች ይገልጻሉ።
ይሁንና በበርካታ የመዲናይቱ ትምህርት ቤቶች ሊካሄድ የታሰበው ሃገር አቀፍ ውይይት ከተሳታፊ መምህራን ዘንድ ያልተጠበቀ ተቃውሞ በማጋጠሙ ምክንያት ውይይቱ የተቋረጠበት አጋጣሚ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።
ከመንግስት የተወከሉ አወያዮች የተለያዩ መረጃዎችን በማቅረብ ላለፉት 25 አመታት በትምህርት ዘንድ ተገኝቷል ያሏቸውን ውጤቶች እያቀረቡ እንደሆነ መምህራን አስታውቀዋል።
መንግስትና መምህራን “ሆድና ጀርባ” ሆነዋል ሲሉ የገለጹት ተሳታፊ መምህራን በውይይቱ መምህራን ድምጸ-ተአቅቦ ለማድረግ የያዙት አቋም በአወያዮች በኩል የማስፈራሪያ ዛቻ እንዲቀርብ ማድረጉን አክለው ተናግረዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ተሳታፊ ያልሆኑ መምህራን ከስራቸው እንዲታደጉ ማሳሰቢያን እያሰራጩ እንደሆነም ታውቋል።
ተመሳሳይ የመምህራት ውይይቶች በሌሎች የክልል ከተሞችም ለሁለት ሳምንት ያህል ጊዜ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከመምህራን ጋር በሚካሄደው ውይይት እንደተጠናቀቀ ተመሳሳይ ውይይቶች ከወላጆችና ተማሪዎች ጋር እንደሚካያሄድ ረቡዕ ይፋ አድርጓል።