በእብናት ወረዳ በተደረገው ተቃውሞ አንድ ወጣት ተገደለ

መስከረም ፭ (አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የእብናት ወረዳ ህዝብ ከመስከረም 1 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ የጀመረውን የስራ ማቆም አድማ ቀጥሎበታል። ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ወታደሮች የከተማው ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። ህዝቡ ማንኛውንም መስዋትነት እንከፍላለን እንጅ ከእንግዲህ በዚህ አገዛዝ ስር አንቀጥልም ማለቱን ተከትሎ ገዢው ፓርቲ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ ወታደሮችን ከእየቦታው አሰባስቦ ወደ እብናት ከተማ እያስገባ ነው።

ትናንት ረቡዕ ከሰአት በሁዋላ 6 የሚደርሱ ወጣቶች በፖለሲኦች መያዛቸውን ተከትሎ የከተማው ህዝብ ሰዎቹ እንዲፈቱ ለመጠየቅ  ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቢያመራም የጠበቀው ግን የጥይት እሩምታ ነው። በዚህ እርምጃ አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በተወሰደው የሃይል እርምጃ የተበሳጨው የከተማው ነዋሪ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ “ የታሰሩት ይፈቱ፣ የማሰሩ ዘመቻ ካልቆመ ስራ አንጀምርም፣  በርሃብ እና በጥይት እያንዳንዳችን እናልቃለን እንጅ ቤታችንንም አንከፍትም” በማለት ለአገር ሽማግሌዎች የተናገሩ ሲሆን፣  ሽማግሌዎችም ይህንኑ መልእክት ማድረሳቸው ታውቋል ።

ወጣቶች ላለመያዝ ሲሉ ሌሊቱን ወደ በረሃ እየወጡ እንደሚድሩ ይናገራሉ።

በደቡብ ጎንደር በሊቦ ከምከም ወረዳ አምቦ ሜዳ ቀበሌ ደግሞ ዛሬ ጠዋት 5 ወጣቶች በወታደሮች ታፍነው ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል። በከተማው ያሉ የደህንነት ሰዎች ወጣቶቹ መንገድ ዘግተዋል ብለው በመጠቆማቸው ከሌላ ቦታ የመጡ ደህንነቶች ወጣቶቹን አፍነው የወሰዱ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች “ ልጆቻችንን ለምን ትወስዳላችሁ?” በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በወገራ ወረዳ አይባ ኪዳነምህረት አካባቢ ትጥቅ ለማስፈታት የሄዱ ወታደሮች ከአርሶአደሮች ያልተጠበቀ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። የጦር መሳሪያቸውን ለማስረከብ ፈቀዳኛ ያልሆኑት አርሰዶሮች በወሰዱት ድንገተኛ እርምጃ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወታደሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዛሬ በርካታ ወታደሮች ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን እና አንዳንድ ሰዎችን እዬያዙ በማሰር ላይ መሆናቸው ታውቋል።