በህዝብ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ አልሰጥም ያለ መኮንን  ከህወሃት ደህንነቶች ጋር ተዋግቶ ህይወቱ አለፈ

መስከረም ፭ (አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- መቶ አለቃ ደጀን ሞቅያለው በሰላም አስከባሪነት ከተሰማራበት ሶማሊያ ወደ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ እንዲዛወር ከተደረገ በሁዋላ፣ በህዝብ ላይ እሱ የሚመራቸው ወታደሮች ምንም አይነት እርምጃ እንዳይወስዱ ማዘዙን ተከትሎ፣ የህወሃት ደህንነቶች ሊይዙት ሲሞክሩ ተታኩሶ ህይወቱ አልፏል።

“ወታደር ድንበር ሊያሰጥብቅ እንጅ ህዝብ ሊገድል ተልእኮ አልተሰጠውም” የሚል ጠንካራ አቋም የነበረው የስማዳ ተወላጁ መቶ አለቃ ደጀን፣ በአካባቢው ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ በስሩ ያሉ ወታደሮች እርምጃ እንዲወስዱ ትእዛዝ እንዲሰጥ ቢጠየቅም፣ አላደርገውም በማለቱ በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ህይወቱ ሲያልፍ፣ በህወሃት ደህንነቶች በኩልም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ደህንነቶች ተገድለዋል።

የመቶ አለቃ ደጀን ጓደኞች ወደ ቤተሰቡ በመሄድ ትናንት መርዶ መናገራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።

መቶ አለቃ ደጀን አገር አረጋጉ ተብሎ ሲገባ ያጋጠመው ሰላማዊ የሆነ ህዝብ መሆኑንና በዚህ ህዝብ ላይ እንዴት ልተኩስ እችላለሁ በማለት ለሚቀርባቸው ሰዎች በመደወል ጭንቀቱን ሲያጋራቸው መቆየቱን  ከጓደኞቹ መካከል አንደኛው ለኢሳት ገልጿል። “ እኔ ከሞትኩ በሁዋላ ይገድላሉ እንጅ እኔ  በህይወት እያለሁ አባሎቼን ህዝብ ግደሉ ብዬ አላዝዝም፣ ምታ ብለው የሚያስገድዱኝ ከሆነ ከእነሱ ጋር ገጥሜ እሞታለሁ” በማለት ለሚቀርባቸው ሰዎች ሲናገር እንደነበር እነዚህ ምንጮች ገልጸዋል።

የመቶ አለቃ ደጀንን መገደል ተከትሎ በህወሃት ደጋፊ ወታደሮች እና በህዝብ ላይ አንተኩስም በሚሉት መካከል መከፋፈል መፈጠሩንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።