መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሁሉቱ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ ውጥረቱ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ በባህርዳር አንዳንድ አካባቢዎች የንግድ
ድርጅቶች ተዘግተው ውለዋል። በሆለታ ሙገር አካባቢም ሱቆችና መዝነኛ ቦታዎች ተዘግተዋል። የዳንኮቴ የስሚንቶ ፋብሪካ መኪኖች እንደማይነቀሳቀሱም የአይን እማኞች ገልጸዋል። በባህርዳር
የስራ ማቆም አድማውን ለማካሄድ የተበተነው ወረቅት በህዝቡ ዘንድ ብዥታን ፈጥሮ ውሎአል። በተወሰኑ ቀበሌዎች የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው አርፍደዋል። አስተባበሪ ሃይሉ ግልጽ መልእክት
ለማስተላለፍ ባለመቻሉ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በፍኖተሰላም አሁንም ውጥረቱ እንዳለ ሲሆን፣ ተጨማሪ ወታደሮች ወደ አካባቢው ተልከዋል። ወታደሮች በድንገት ወደ አርሶአደሮች ቤት በመሄድ መሳሪያ እያስፈቱ መሆኑ ታውቋል።
በሰሜን ጎንደር እብናት ወረዳ ደግሞ የልዩ ሃይል አባላት ከአጋዚ ወታደሮች ጋር መስማማት አልቻሉም። የልዩ ሃይል አባላት አካባቢያቸውን እራሳቸው መጠበቅ እንደሚችሉ በመግለጽ፣
ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ በመጠየቅ ላይ ናቸው። በደብረታቦር መደበኛ ፖሊሶች ከስራ ታግደው ጥበቃው በአጋዚ ወታደሮች እየተካሄደ ነው።
በብርሸለቆ የታሰሩት ወጣቶች እታ ፋንታ አለመታወቅ የክልሉን ህዝብ እያበሳጨ ሲሆን፣ ልጆቻቸው የታሰሩባቸው ወላጆች ወደ ብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመሄድ ልጆቻችን የት
እንዳሉ ንገሩን በማለት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የእስር ቤት ጠባቂዎች “ ያሰሩዋቸው ወታደሮች እንጅ እኛ አይደለንም፣ እነሱን ጠይቁ” በማለት መልስ እየሰጡ መሆኑን ወላጆች ገልጸዋል።