ኢሳት (መስከረም 2 ፥ 2009)
በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ በመካሄድ ላይ ባለው የፓራ ኦሎምፒክ በ 1ሺ 500 ሜት የብር ሜዳልያን ያገኘው ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምሩ ደምሴ በመንግስት የሚፈጸሙ ግድያዎችን በመቃወም የአትሌት ፈይሳ ሌሊሳን ድርጊት መድገሙ አለም አቀፍ መገኛና ብዙሃን ከስፍራው ዘገቡ።
ሰኞ በውድድሩ ሜዳልያን ለማግኘት የበቃው አትሌቱ በአለም አቀፉ ደረጃ ተመሳሳይ መልዕክትን ካስተላለፉ አትሌቶች መካከል አራተኛው ለመሆን መብቃቱን ኢንዲፔንደንት የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
አትሌቱ እጁን በማጣመር በድሉ ወቅት ያስተላለፈው መልዕከት በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸሙ ግድያዎችንና አፈናዎችን ለመቃወም የሚያመለክት መሆኑን ጋዜጣው በአትሌቱ ድርጊት ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አቅርቧል።
አትሌት ታምሩ ደምሴ ሜዳሊያውን ለማግኘት በበቃበት ወቅት ያስተላለፈውን ፖለቲካዊ መልዕክት በሜዳሊያ አቀባባል ስነስርዓቱ ወቅትም መድገሙ ታውቋል።
ባለፈው ወር አትሌቱ ፋይሳ ሌሊሳ የማራቶን ውድድሩን በሁለተኛነት ባጠናቀቀ ጊዜ ተመሳሳይ ተቃውሞን አንጸባርቆ ድርጊቱ በአለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል።
ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን አድርጎ የነበረው አትሌት ፈይሳ ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሃገር ቤት የሚካሄዱ ግድያዎችን አፈናዎችን በመቃወም ተመሳሳይ ድርጊትን እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር የሚታወቅ ነው።
አትሌቱ የወሰደውን ድርጊት ተከትሎ በተለያዩ የአለማችን ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ150 ሺ ዶላር በላይ መዋጮን በማድረግ ለአትሌቱ ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ የሰነበቱ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት ወደዚህ አሜሪካ የገባው አትሌት ፈይሳ ማክሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
እሁድ ምሽት በሪዮ ፓራ ኦሎምፒክ ብርን ለማገኘት የበቃው አትሌት ታምሩ፣ በ1ሺ 500 ሜትር ፈጣን ሰዓት ጭምር ማስመዝገቡን ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ አስነብቧል።