በኢድ አል አደሃ አረፋ አከባበር ላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰሙ

መስከረም ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- 1 ሺህ 437ኛው የኢድ አል አደሃ አረፋ በአል በመላው አገሪቱ በሰላምና በተቃውሞ ተከብሯል። በአዲስ አበባ በአሉ ያለምንም ችግር የተከበረ ሲሆን፣ በጎንደር፣ ድሬዳዋ፣ አወዳይና ሻሸሜ ህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞውን አሰምቷል።

በጎንደር ከተማ ሙስሊሙ በአሉን ለማክበር በወጣበት ወቅት በመላው አገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ግድያ በጽኑ የሚያወግዙ መፍክሮችን ከማሰማት በተጨማሪ  ለኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ያለውን አጋርነት  እጆቹን አጠምሮ በማሳየት ገልጿል። ቀይ ካርዶችን በማሳየት በስልጣን ላይ ያለውን ገዢ ቡድን በቃህ ብሎአል።

የአጋዚ ወታደሮች ባዶ እጁን ለጸሎት በወጣው ህዝብ ላይ በወሰዱት የሃይል እርምጃ በርካታ ሰዎች ተገዶድተዋል። ቁጥራቸው በውል ያልተወቀ ወጣቶችም ተይዘው ታስረዋል። በድሬዳዋ፣ አወዳይ፣ ሻሸመኔም እንዲሁመህዝበ ሙስሊሙ ተመሳሳይ ተቃውሞ አሰምቷል። የከተማው ከንቲባ ንግግር በሚጀምሩበት ወቅት፣ በበአሉ ላይ የተገኘው ሁሉ በአንድነት የተለያዩ የውግዘት ቃሎችን ከ30 ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ አሰምቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ከእስር ቤት በመውጣታቸው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው። ገዢው ፓርቲ የደረሰበትን ውጥረት ለማስተንፈስ የኮሚቴ አባላቱን በምህረት የለቀቀ ቢሆንም፣  መሪዎቹ ይቅርታ ጠይቀው እንደተፈቱ አድርጎ ያሰራጨው መረጃ ግን ብዙዎችን አበሳጭቷል።

ከእስር የተለቀቁት መሪዎች ኡስታዝ አቡበክርን፣  ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ ኡስታዝ በድሩ ሁሴን፣  መከተ ሙኄ፣ ኡስታዝ ሰኢድ አሊ፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው፣  ሙባረክ አደም፣ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ፣ ኡስታዝ ሙራድ ሹኩር እና መሬም ሃያቱ ይገኙበታል።

በሌላ በኩል በሳውድ አረቢያ የሚኖሩት ሼህ  ሰኢድ አህመድ ሙስጠፋ ሙስሊም ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። ሼህ ሰኢድ ፣ የኮሚቴው አባላት ቀድሞውንም መታሰር እንዳልነበረባቸው ገልጸው፣ ሙስሊሙ ጥያቄዎቹ ያልተመሰሉ በመሆናቸው ትግሉን አጠንክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የመጀመሪያውን መግለጫ አውጥቷል።