በኦሮሚያ ክልል ከቤት ያለመውጣት አድማ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ኢሳት (ጳጉሜ 4 ፥ 2008)

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ከቀናት በፊት የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት የስራ ማቆም አድማ አርብ ድረስ መቀጠሉን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስታወቁ። የአዲስ አበባ ኮሚሽን በበኩሉ የፊታችን እሁድ የሚከበረውን የአዲስ አመት በአል ዝግጅት በሰላም ለማክበር ሲባል በከተማዋና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የጸጥታ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን አርብ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ ግድያዎችንና አፈናዎችን በመቃወም ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አምቦ ከተማና ሌሎች አካባቢዎች የተጀመረው ሁለገብ አድማ አርብ ድረስ መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በሻሸማኔ አምቦና ጉዳር እንዲሁም በወለጋ ነቀምቴ ዙሪያ ስር በሚገኙ የተለያዩ የዞን ከተሞች የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው መሰንበታቸውንና በየከተሞቹ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራ ማቆማቸው ለመረዳት ተችሏል።

የክልሉ ባለስልጣናት የንግዱ ማህበረሰብ ተቃውሞ እንዲያበቃ የተለያዩ ማሳሰቢያዎችን ቢያሰራጩም ህዝቡ በእምቢተኝነቱ መቀጠሉ ታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ እሁድ የሚከበረውን የ2009 አዲስ አመት አከባበርና የአረፋ በዓልን በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በሚል በመዲናይቱ አዲስ አበባ የጸጥታ ቁጥጥሩ መጠናከሩ አርብ ገልጿል።

የጸጥታ አባላት በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች በግልጽና በስውር እንዲሰማሩ ተደርጓል ሲል በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድሮ የሚከበረው የአዲስ አመት በዓል ውጥረትና ያለመረጋጋት ሁኔታ የታየበት መሆኑንና የንግዱ እንቅስቃሴ ከተለመደው ውጭ መቀዛቀሱን ተናግረዋል።

ከተለያዩ ከተሞች ለበዓሉ አካባበር ወደ አዲስ አበባ ይገቡ የነበሩ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጣሸቀጦች በተገቢው መጠን ሳይገቡ መቅረታቸውንና በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ማሳደሩ በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃንና ነዋሪዎች አመልክተዋል።