ጳጉሜ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአይን እማኞች እንደገለጹት በሰሜን ጎንደር ዞን ሽንፋ እና ሸይዲ መሃል ላይ ዘውዴ ባድማ በሚባል ቦታ ላይ የአጋዚ ወታደሮች ከልዩ ሃይል
አባላት ጋር በጋራ በመሆን፣ የህዝቡን የጦር መሳሪያ ለመቀማት ሲንቀሳቀሱ መሳሪያቸውን ለማስረከብ ፈቀዳኛ ካልሆኑት ነዋሪዎች ጋር ተታክሱዋል። የተኩስ ልውውጡን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር
ያለው ሰራዊት ወደ አካባቢው ተንቀሳቅሷል።
ህዝቡ መሳሪያውን ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ገዢው ፓርቲ በጉልበት መሳሪያ ለመቀማት ወስኗል። በሰሜን ጎንደር ባሉ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች የስልክ ኔትወርክ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ
ሲሆን፣ የአንድ አካባቢ ህዝብ ከሌላው አካባቢ ህዝብ ጋር እንዳይገናኝ በመደረጉ ህዝቡ እንደ ወትሮው ከያካባቢው ተጠራርቶ ጥቃቱን ለመቋቋም እንቅፋት ፈጥሮበታል።
ዛሬ በተካሄደው ግጭት ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ መረጃ ባይደርሰንም፣ ትናንት ምሽት ጎንደር ውስጥ የፌደራል ፖሊሶች ተገድለው መገኘታቸው ታውቋል። ይህን ተከትሎ አዘዞ አካባቢ ምሽት
ላይ ከፍተኛ ጥበቃ ሲካሄድ አምሽቷል። በርካታ ወጣቶችም ተይዘው ታስረዋል። የፌደራል ፖሊሶችን ማን እንደገደላቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የመሳሪያ መቀማቱ እንቅስቃሴ በጎጃምም የተጀመረ ሲሆን፣ በተለይ የጦር መሳሪያ በብዛት አለባቸው ተብሎ በሚገመቱት የሸበል በርንታና አካባቢዋ ትጥቅ የማስፈታቱ እንቅስቃሴ ቢጀመርም፣
ህዝቡ ግን መሳሪያውን ለማስረከብ ፈቃደኛ አልሆነም።
ከዘመን መለወጫ በአል በሁዋላ ህዝቡ ተቃውሞውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል በሚል ስጋት በርካታ ወጣቶች እየታፈኑ በመታሰር ላይ ናቸው።
በብርሸለቆ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ታስረው ስቃይ እየደረሰባቸው ሲሆን፣ አሁንም ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች ወደ እስር ቤቱ በመጓዝ ላይ ናቸው። በድብደባ ብዛት፣
በህመም እና በእባቦች ተነድፈው የሞቱ ወጣቶች መኖራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።