ኢሳት (ጳጉሜ 3 ፥ 2008)
ሰሞኑን በተለያዩ የአማራና የኦሮሚያ የክልል ከተሞች የተጀመረው የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ መቀጠሉ ታውቋል።
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙት የአምቦና አካባቢዋ የንግድ ድርጅቶችን የመዝጋቱ ተቃውሞ ሃሙስ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉን ከሃገር በት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በሻሸማኔ ከተማ እንዲሁም በምስራቅና ምዕራብ ኦሮሚያ ስር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የአገልግልት መስጫ ተቋማት ስራቸው ተስተጓጉሎ መቀጠሉን ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።
በምዕራብ ሃረርጌ ስር በምትገኘው የሂርና ከተማና አካባቢዋ ሃሙስ በነዋሪዎችና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ግጭት መቀስቀሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በአግባቡ ባልታወቀ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።
የክልሉ ባለስልጣናት በሁለቱ ክልሎች ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው ከቤት ያለመውጣትና የስራ ማቆም አድማ እንዲያበቃ የማሳሰቢያ መልዕክቶችን ቢያሰራጩ ነዋሪው በአድማው መቀጠሉን ከህገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።