ኢሳት (ጳጉሜ 3 ፥ 2008)
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ በደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ጉብኝንትን እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች በሃገሪቱ በሚያደርጉት የ19 ቀናቶች ቆይታ የፖለቲካ አመራሮችን የማህበረሰብ ተወካዮችንና ስደተኞችን እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመገናኘት ውይይት እንደሚያካሄዱ ታውቋል።
በደቡብ ሱዳን ያለው ግጭት ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት መሆኑን ሲገልፅ የቆየው ኮሚሽኑ በኢትዮጵያና በዩጋንዳ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስጋት እየሆኑ መምጣታቸው ሲያስታውቅ መቆየቱ ይታወሳል።
በኮሚሽኑ የተወከሉ የሰብዓዊ መብት መርማሪ ባለሙያዎች ከፓርላማ አባላት ከጸጥታ ሃይሎች እንዲሁም የፍትህ አካላት ጋር አበይት በመሆን የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ለቀናት የሚቆይ ምክክርን በየሃገሪቱ ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሶስቱ ሃገራት ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሚመረምሩት የኮሚሽኑ ልዑካን አባላት በፈረንጆቹ አዲስ አመት መግቢያ ላይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ሪፖርትን እንደምያቀርቡም ለመረዳት ተችሏል።
የልዑካን ቡድኑ በተያዘው ሳምንት በደቡብ ሱዳን ግብኝት እንደሚጀምሩ ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞና በአማራ ክልል ባለፈው ወር የተቀሰቀሰውን ተመሳሳይ ድርጊት ተከትሎ ከ500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይገልጻሉ።
የአሜሪካ መንግስት ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ አካላት ይህንኑ ድርጊት በመኮነን መንግስት የሃይል ዕርምጃን ከመውሰድ እንዲቆጠብ እያሳሰቡ ይገኛል።