የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ኮንሶ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ የእሳት ቃጠሎ ማድረሳቸው ተነገረ

ኢሳት (ጳጉሜ 3 ፥ 2008)

በደቡብ ክልል በሚገኘው የሰገን ህዝቦች  ስር የሚገኙ የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት በቅርቡ ያቀረቡትን አስተዳደራዊ ጥያቄ ተከትሎ ከቀናት በፊት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በዘጠኝ ቀበሌዎች የእሳት ቃጠሎ አደጋ መድረሱን ለኢሳት አስታወቁ።

በዘጠኙ ቀበሌዎች የደረሰውን ይህንኑ የእሳት አደጋ ተከትሎም ከ1ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት በልዩ ወረዳ ወይም በዞን እንዲቋቋሙ አስተዳደራዊ ጥያቄን ቢያቀርቡም ምላሻቸው በክልሉ መንግስት ይሁንታ መነፈጉ ይታወሳል።

በአካባቢው አሁንም ድረስ ውጥረት መኖሩን የሚናገሩት ነዋሪዎች አስተዳደራዊ ጥያቄ አቅርበዋል በተባሉ የብሄረሰቡ አባላት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት በመንግስት አካላት ተፈጽሟል ባሉት በዚህ ጥቃት በዘጠኝ ቀበሌዎች መጠነ ሰፊ የእሳት ቃጠሎ መድረሱንና ከ1 ሺ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።

በየቀበሌው እስከ 150 የሚደርሱ አባወራዎች እንደሚኖር ያስረዱት እማኞች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያኖችና ሌሎች መጠለያዎች በጊዜያዊነት ተጠልለው እንደሚገኙ ለኢሳት ገልጸዋል።

በዞኑ ከተጠልሉት ነዋሪዎች በተጨማሪ በርካታ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ክልሎችና ቀበሌዎች መፈናቀላቸውን ለዜና ክፍላችን እማኝነትን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

የኮንሶ ብሄረሰብ አባላት በተለያዩ ጊዜያት አስተዳደራዊ ጥያቄ በማቅረብ የክልሉና የፌዴራል ባለስልጣናት በወረዳ ወይም በዞን ደረጃ እንዲያቋቁማቸው ሲጠየቁ ሰንብተዋል።

የደቡብ ክልል መንግስት የብሄረሰቡ አባላት የቀረቡት አስተዳደራዊ ጥያቄ ተገቢ አይደለም በማለት ውድቅ ቢያደርገውም፣ የብሄረሰቡ አባላት አሁንም ድረስ ምላሽ እንዲያገኙ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ይሁንና የብሄረሰቡ አባላት እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ ተከትሎ በመንግስት ተወካዮች ሃላፊዎች ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉ መንግስት የሰጠው ምላሽ የለም።