ጳጉሜ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል የአገር ሽማግሌዎችን እየሰበሰበ ከእንግዲህ ወጣቶችን እንደማያስርና ያሰራቸውን እንደሚፈታ ቃል ቢገባም በሌላ በኩል አሁንም ወጣቶችን በብዛት እየያዘ ወደ ብርሸለቆ እያጋዘ ነው።
በብርሸለቆ ወታቶች በርሃብና ውሃ ጥም እየተሰቃዩ ሲሆን፣ በባዶ እግራቸው በጠርሙስና እሾህ ላይ እንዲራመዱ እንደሚደረጉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ወጣቶች የሚደርስባቸውን እንግልት ተቋቁመው አሁንም በእስር ቤት ውስጥ የነጻነት መዝሙሮችን እንደሚዘምሩ፣ በዚህ ድርጊታቸው ጠባቂዎች እየተናደዱ ጥቃታቸውን እንደሚጨምሩባቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ህወሃት ሆን ብሎ በአማራ ክልል የሚማሩ የትግራይ ተማሪዎች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ እያደረገ ነው። መደበኛ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በፌደራል መንግስት በኩል የድጋፍ ወረቀት እየተሰጣቸው መልቀቂያ በማውጣት ላይ ናቸው።